ኢትዮጵያ በረጅም ዘመናት ታሪኳ ውስጥ በየብስ ብቻ ሳይሆን በባሕርም ላይ የተገነባ የሥልጣኔ፣ የንግድ እና የመከላከያ ታሪክ ያላት ሀገር ናት።
ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር እና በሕንድ ውቅያኖስ የንግድ መስመሮች ላይ ለዘመናት የተጫወተችው ሚና የኢትዮጵያን የባሕር ታሪክ የሚያሳይ ጉልህ ማስረጃ ነው።
በእነዚህ ጊዜያት የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል የቀጣናውን የባሕር ደኅንነት በማስጠበቅ የማይተካ ሚና ተጫውቷል።
በተለይም በቀይ ባሕር አካባቢ የሚደረጉ የንግድ እንቅስቃሴዎችን ከስጋት ለመጠበቅ፣ የባሕር ወንበዴነትን ለመከላከል፣ የኢትዮጵያን የባሕር ላይ ሉዓላዊነት ለማስከበር እና የአካባቢውን መረጋጋት ለማስጠበቅ የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል ያከናወናቸው ተግባራት በወታደራዊ ታሪክ ውስጥ በክብር የሚታወሱ ናቸው።
በወቅቱ በአፍሪካ ውስጥ በጥራት፣ በሥልጠና እና በተግባራዊ ብቃት ከሚጠቀሱ የባሕር ኃይሎች መካከል አንዱ ነበር።
ሆኖም የታሪክ አጋጣሚዎች፣ የፖለቲካ ሴራዎች እና የውጭ እና የውስጥ ታሪካዊ ጠላቶች የፈጠሯቸው ውስብስብ ሁኔታዎች ኢትዮጵያን ከራሷ እና ከታሪካዊው ግዛቷ አርቀዋት ቆይተዋል።
ለዓመታት በጀግንነት ያገለገለው ተቋም በሴራ ከሥራ ውጪ ሆኖ ቢቆይም የባሕር ታሪኩ እና ወታደራዊ አቅሙ ግን ፈጽሞ አልጠፋም ነበር።
የውስጥ እና የውጭ ታሪካዊ የኢትዮጵያ ጠላቶች ኢትዮጵያን ከባሕር በማግለል የኢኮኖሚ፣ የንግድ እና የደኅንነት ጫና ውስጥ ያስገቧት ሲሆን፣ በዓለም ላይ ከፍተኛ የሕዝብ ብዛት ካላቸው ሀገራት አንዷ ሆና የባሕር በር አልባ መሆኗ የንግድ ወጪን ከፍ አድርጎ የብሔራዊ ጥቅሞቿን አስጠባቂ የሆነ የባሕር አቅም እንዳይኖራት አድርገዋል።
ይሁን እንጂ የባሕር ኃይሉ ታሪክ በዚያ አላበቃም። በቅርብ ዓመታት ኢትዮጵያ የባሕር ኃይሏን እንደገና ለማደራጀት የጀመረችው ጥረት በኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ ስትራቴጂካዊ ዕይታ ውስጥ ትልቅ ቦታ ይይዛል።
የባሕር ኃይሉ እንደገና መቋቋሙ ብቻ ሳይሆን የሰው ኃይል ሥልጠና፣ የቴክኖሎጂ አቅም ግንባታ እና ከወዳጅ ሀገራት ጋር የሚደረጉ የደኅንነት ትብብሮች በቀጣናው የባሕር ደኅንነት ላይ ኢትዮጵያ ዳግም ንቁ ተሳታፊ እንድትሆን እያስቻሉ ነው።
ዛሬ የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል በቀጣናው የደኅንነት አወቃቀር ውስጥ የሚኖረውን ሚና በአዲስ መልኩ እየገነባ ይገኛል። የቀይ ባሕር የዓለም ንግድ ወሳኝ መተላለፊያ ከመሆኑ አንጻር ኢትዮጵያ በዚህ አካባቢ ሰላም እና መረጋጋት እንዲጠበቅ ያላት ፍላጎት እና የምትወስዳቸው እርምጃዎች ከሀገራዊ ጥቅም ባሻገር ለክልሉም ደኅንነት አስፈላጊ ናቸው።
ታሪክ እንደሚያስረዳን የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል የአንድ ወታደራዊ ተቋም ብቻ ታሪክ አይደለም፤ የሀገር ሉዓላዊነት፣ የስትራቴጂያዊ ራዕይ እና የትውልዶች ጽናት ምልክት ነው።
ከታሪካዊ ጀግንነቱ እስከ አሁናዊ ዳግም መቋቋሙ ድረስ የባሕር ኃይሉ ያሳየው ጉዞ ኢትዮጵያ በቀጣናው ደኅንነት እና በባሕር ጉዳዮች ውስጥ አሁንም ያላት ስፍራ ትልቅ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው።
በሀብተሚካኤል ክፍሉ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: