Search

ኢትዮጵያና ወደቦቿ፡ ከትላንት እስከ ዛሬ

ሓሙስ ሐምሌ 30, 2018 47

የኢትዮጵያ ታሪክ ገፆች ሲገለጡ ጎልተው ከሚታዩት አንዱ የባህር በሮቿ ጉዳይ ነው። ታሪክ እንደሚመሰክረው፣ የሀገሪቱ የዕድገትም ሆነ የመዳከም ዘመናት በቀጥታ ከባህር በሮቿ ባለቤትነት ጋር የተሳሰሩ ናቸው።

"ኢትዮጵያ በታሪኳ ያለፈቻቸው መነሳትና መውደቅ ከባህር ጋር ከነበራት ቅርበትና ርቀት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አለው" የሚለው የፕ/ ሹመት ሲሻኝ አባባል የዚህን ሐቅ ክብደት ያጎላዋል።

ኢትዮጵያ በታሪኳ ያለፈችባቸው የመነሳትና የመውደቅ ምዕራፎች ከባህር ጋር ከነበራት ቅርበትና ርቀት ጋር ቀጥተኛ ቁርኝት አላቸው።

የባህር በሮቿ በእጇ በነበሩበት ዘመን የበለፀገችና የጎለበተች አገር መገንባት ስትችል፣ በተነጠቀችባቸው ዘመናት ደግሞ ኢኮኖሚዋ የኮሰሰበትንና ፖለቲካዋ የተናጋበትን ጊዜ አሳልፋለች። ይህንንም ሐቅ የጥንት ወደቦቿ ታሪክ ቁልጭ አድርጎ ያሳየናል።

አዱሊስ፡ የጥንቱ ዓለም የንግድ ማዕከል የወደብ ጥቅም በተደራጀና በሰፋ መልኩ በሀገራችን ጥቅም ላይ መዋል የጀመረው በአክሱማውያንና ከእነሱም በፊት በነበሩት የዳማት ነገሥታት ዘመን ነው።

አዱሊስ በቀይ ባህር ጠረፍ ላይ የተንሰራፋች፣ አክሱማውያን ገናና ከነበሩት የግሪክና የባዛንታይን ነገሥታት ጋር የሚገናኙባት ወርቃማ በር ነበረች።

የግሪኩ ጸሐፊ ‹‹ፕሊኒ ትልቁ›› (Pliny The Elder) አዱሊስን ዐቢይ ገበያ ለትሮግሎዳይትና ለኢትዮጵያ ሕዝቦች ሲል የገለጻት ሲሆን፣ የዳማትና የአክሱም ነገሥታት መንግሥታቸውን ገናና ያደረጉት በዚህ ወደብ በሚያገኙት ገቢ እንደነበር አትቷል።

የኢትዮጵያ ነገሥታት በወቅቱ ዕጣን፣ ወርቅ፣ የከበሩ ድንጋዮችና የአደን ዱር አራዊት ቆዳ በማውጣት ከፍተኛ የንግድ ልውውጥ ያደርጉ ነበር።

‹‹ኮስሞስ›› የተባለው ጸሐፊም አዱሊስን በጎበኘበት ወቅት፣ አፄ ካሌብ ቀይ ባህርን ተሻግረው የመንንና ደቡብ ዓረቢያን ለመቆጣጠር የሚያስችል እጅግ የዳበረ የባህር ኃይል እንደነበራቸው አስፍሯል። አዱሊስ እስከ ስምንተኛው ክፍለ ዘመን ድረስ የኢትዮጵያ የብልፅግና ማማ ሆና አገልግላለች።

ምጽዋ፡ የላሊበላ ራዕይና የቱርኮች ሴራ ከአክሱም መዳከምና ከኦቶማን ቱርኮች መስፋፋት በኋላ የኢትዮጵያ የባህር ትኩረት ወደ ምጽዋ አቅንቶ ነበር።

ቱርኮች በአካባቢው በነበሩት የቤጃ ሕዝቦች ላይ ጫና ፈጥረው ከተማዋን እንደ ጦር ካምፕ ቢጠቀሙባትም፣ የዛግዌው ንጉሥ ቅዱስ ላሊበላን ጨምሮ የኢትዮጵያ ነገሥታት ይህችን ወደብ ይፈልጓት ነበር።

ንጉሥ ላሊበላ ወደ ኢየሩሳሌም ለማድረግ ላሰቡት ጉዞ በምጽዋ በኩል ያጋጠማቸው የቱርኮች ማነቆ፣ አዲሲቱን ኢየሩሳሌም በኢትዮጵያ ምድር (ሮሃ) እንዲያንፁ ምክንያት እንደሆናቸው ታሪክ ጸሐፊዎች ይገልጻሉ።

ምጽዋ ከጊዜ በኋላም 90 በመቶ የሚሆነውን የኢትዮጵያ የወደብ አገልግሎት ስትሰጥ የኖረችና የኢትዮጵያ የባህር ኃይል ዋና ማዕከል የነበረች ታላቅ ወደብ ናት።

ዘይላ እና በርበራ፡ የህንድ ውቅያኖስ በሮች በኦቶማን ቱርኮች በቀይ ባህር በኩል እንቅፋት ሲፈጠርባቸው፣ የኢትዮጵያ ነገሥታት ፊታቸውን ወደ ህንድ ውቅያኖስ በሮቻቸው፣ በተለይም ወደ ዘይላ አዞሩ።

በወቅቱ በርካታ ቋንቋዎችን አቀላጥፈው የሚናገሩትና የንግድ ተሰጥዖ የነበራቸው የአርጎባና የአፋር ነጋዴዎች፣ ዘይላን የኢትዮጵያ ዋና የንግድ ማስተላለፊያ ወደብ አድርገዋት ነበር።

ይህንን የተገነዘቡት ቱርኮች በአካባቢው የነበሩ መሪዎችን በማነሳሳት የኢትዮጵያን የንግድ መስመር ለማዘጋት ሞክረዋል፤ እንግሊዛዊው ተጓዥ ጄምስ ብሩስ እንደሚለው የግራኝ አህመድ ጦርነት ጥንስስ የተጀመረው ከዚሁ የወደብ ንግድ ሽኩቻ ጋር ተያይዞ ነው።

18ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ደግሞ ምስራቅ ኢትዮጵያ (ሐረር) በማዕከላዊ መንግሥት ቁጥጥር ሥር ከዋለ በኋላ፣ የዛሬዋ ሶማሌላንድ ሁለተኛ ከተማ የሆነችው ‹‹በርበራ›› ለኢትዮጵያ ከፍተኛ የወደብ አገልግሎት መስጠት ጀመረች።

በርበራን ነጋዴዎች የመረጡበት ዋናው ምክንያት አየሯ ከሌሎቹ አካባቢዎች አንፃር ቀዝቀዝ የሚልና ለንግድ እንቅስቃሴ ምቹ በመሆኑ ነበር።

ዳግማዊ አፄ ምኒሊክ የዘይላን ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ሲገልጹ፣ ለጣሊያኑ ንጉሥ ኡምቤርቶ በላኩት ደብዳቤ ላይ የዘይላን በር ነገር በሚቻልዎ ነገር ሁሉ ተጣጥረው በእኔ እጅ ቢሆን እንኳን... በዘይላ አደርገው ነበር፤ በማለት የወደብን ወሳኝነትና ብሔራዊ ስሜትን አንፀባርቀዋል።

ታጁራ እና ጅቡቲ (ኦቦክ) የፈረንሳይ ኩባንያ ይዞት የነበረው የታጁራ ወደብም የኢትዮጵያን ንግድ ሲያስተናግድ ቆይቷል። ይሁንና በታጁራ በነበረው እጅግ ሞቃታማ የአየር ጠባይ ምክንያት ፈረንሳዮች አካባቢውን ለቀው ‹‹ኦቦክ›› (የዛሬዋ ጅቡቲ) ላይ ሰፈሩ።

ዳግማዊ አፄ ምኒሊክ የዚህን ስትራቴጂካዊ ቦታ ጠቀሜታ በመረዳት ከፈረንሳይ ጋር ስምምነት በማድረግ ጅቡቲን ዋነኛ የኢትዮጵያ ወደብ አድርገው ተጠቀሙባት፤ ለዚህም ሲባል ታሪካዊውን የኢትዮ-ጅቡቲ የምድር ባቡር መስመርን አስገነቡ።

የጋምቤላ ወደብ፡ የምዕራቡ የውሃ በር የኢትዮጵያ የወደብ ባለቤትነት በምሥራቅ ብቻ የተወሰነ አልነበረም። ምኒሊክ የደቡብና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያን ወደ ማዕከላዊ መንግሥት ሲያጠቃልሉ፣ በባሮ ወንዝ ላይ የሚገኘውን የጋምቤላ ወደብ አስተውለው ነበር።

እንግሊዞች ሱዳንን ሲያስተዳድሩ ቦታውን ይጠቀሙበት የነበረ ሲሆን፣ ምኒሊክ ቦታው የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ግዛት መሆኑን በማስረገጥ ለአገልግሎቱ ቀረጥ ማስከፈል ጀመሩ።

የጅማው ንጉሥ አባ ጅፋርም በዚህ ወደብ በኩል ቡና፣ የዝሆን ጥርስና የዱር እንስሳት ቆዳ ወደ ውጭ በመላክ ለኢትዮጵያ ከፍተኛ ገቢ ያስገኙ ነበር። የኢትዮጵያን የተፈጥሮ የወደብ አማራጭነት በተግባር ያሳየ ታሪካዊ ሥፍራ ነው።

አሰብ፡ ታሪካዊው ሐቅ እና ያልተቋጨው ጥያቄ አሰብ በደቡባዊ ቀይ ባህር ጫፍ የሚገኝ፣ የአፋርና የአርጎባ ሕዝቦች ታሪካዊ መኖሪያ የሆነ ሰፊ የባህር ዳርቻ ነው። አሰብን ጣሊያናዊው ጁሴፔ ሳፔቶ ‹‹ሩባቲኖ›› ኩባንያ የገዛው ከአፋሩ ሱልጣን ኢብራሒም እንጂ አካባቢው የኤርትራ አካል ሆኖ አልነበረም።

ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላም እንግሊዞች አሰብን ለኢትዮጵያ አስቀርተው ሌላውን ለመከፋፈል ሞክረው ነበር።

በደርግ ዘመን አሰብ እጅግ ዘመናዊ መሠረተ ልማቶች፣ ዘመናዊ አውሮፕላን ማረፊያ እና የነዳጅ ማጣሪያ የተገነባላት የኢትዮጵያውያን የልብ ትርታ ሆና ነበር።

1983 .. በተፈጠረው የፖለቲካ ሥልጣን ሽግግርና የሰሜን ጦርነት ኢትዮጵያውያን ዜጎች ከአሰብ ሲፈናቀሉ፣ ሀገሪቷም ታሪካዊና ሕጋዊ የባህር በሯን ተነጠቀች።

65 ኪሎ ሜትር ያነሰ ርቀት ከባህር እያላት፣ ዛሬ ላይ 130 ሚሊዮን ሕዝብ አገር ወደብ አልባ ሆና ቀርታለች። በሌላ በኩል ደግሞ አሰብ ዛሬ ላይ ምንም ዓይነት የንግድ እንቅስቃሴ የማይታይባት፣ አገልግሎት አልባ "የመናፍስት ከተማ" (Ghost City) ሆና ትገኛለች።

የወደብ ትንሣኤ ኢትዮጵያ የዓለም አርባ ወደብ አልባ አገራት መሪ መሆኗ የተፈጥሮ ወይም የታሪክ ብያኔ ሳይሆን፣ በውስጥ ድክመትና በፖለቲካዊ ሻጥር የተፈጠረ የአጭር ጊዜ የታሪክ ግርዶሽ ነው።

ከላይ የተዘረዘሩት የአዱሊስ፣ የምጽዋ፣ የዘይላ፣ የበርበራ፣ የታጁራ፣ የጋምቤላና የአሰብ ታሪኮች የሚያረጋግጡት፣ ኢትዮጵያ ለዘመናት የባህር በር ባለቤት እንደነበረችና ከዓለም ጋር በራሷ በር ስትገበያይ እንደኖረች ነው።

አዲሱ ትውልድ ይህንን አጭር የወደብ ማጣት ታሪክ የሚቋጭበትና የወደብ ትንሣኤን እውን የሚያደርግበት ታሪካዊ ምዕራፍ ላይ ይገኛል። የጠፋውን የባህር ላይ ክብር ለማስመለስ የሚደረገው ግስጋሴ፣ የሀገር ህልውናን፣ የኢኮኖሚ ብልፅግናን እና የቀጣናውን የጋራ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ዓላማ ያደረገ፣ የማይቆም የፍትሕና የታሪክ ጥሪ ነው!

በአዶኒያስ ወልደአረጋይ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: