Search

ከንድፈ ሐሳብ ወደ ተግባር የተሸጋገረው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር

ሓሙስ ሐምሌ 16, 2018 103

ታዋቂው ጀርመናዊ ፈላስፋ ዩርገን ሃበርማስ በምክክራዊ ዴሞክራሲ ንድፈ ሐሳቡ የፖለቲካ ውሳኔዎች ቅቡልነት የሚያገኙት ዜጎች ያለጫና እና ያለተፅዕኖ በእኩልነት የሚሳተፉበት እና በነፃነት ሐሳብ የሚለዋወጡበት "ምቹ የውይይት ሁኔታ" ሲፈጠር መሆኑን ያስረዳል።

በዚህ ንድፈ ሐሳብ መነጽር ሲታይ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን እያካሄደ ያለው ሂደት ሰፊ ሕዝባዊ ተሳትፎን መሠረት ያደረገ፣ በውይይት እና በምክንያታዊ መግባባት ላይ የተመሰረተ አካታች የምክክር ሂደት ለመገንባት ያለመ ጥረት መሆኑን ያሳያል።

ለረጅም ዘመናት የኢትዮጵያ ፖለቲካ በጥቂት ልሂቃን የውሳኔ አሰጣጥ እና በጠመንጃ አፈሙዝ የበላይነት በተደገፈ አካሄድ ሲመራ ቆይቷል።

የሀገራዊ ምክክሩ ሂደት ግን ይህንን አካሄድ በመቀየር ዜጎች በቀጥታ በሚሳተፉበት፣ ሐሳባቸውን በነፃነት በሚያቀርቡበት እና በምክንያታዊ ውይይት የጋራ መፍትሔ በሚፈልጉበት መድረክ እየተገነባ ይገኛል።

የምክክሩ አካታችነትም በተግባር እየተረጋገጠ ይገኛል። የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ ምክር ቤታቸው በኩል በመሳተፍ ሀገራዊ ጉዳዮችን ከሰፊ እይታ አንፃር እየመከሩ ነው።

አርሶ አደሮች እና አርብቶ አደሮች የመሬት እና የተፈጥሮ ሀብት ጉዳዮችን በቀጥታ ወደ አጀንዳ አምጥተዋል።

እንዲሁም የሃይማኖት አባቶች፣ አባገዳዎች እና ሌሎች ሀገር በቀል የማኅበረሰብ መሪዎች የእርቅ እና የመግባባት እሴቶችን ወደ ሂደቱ አምጥተዋል።

በሌላ በኩል ሴቶች፣ ወጣቶች፣ አረጋውያን እና አካል ጉዳተኞች የእኩልነት፣ የተወካይነት እና የተደራሽነት ጉዳዮች በሀገራዊ አጀንዳ ላይ እንዲካተቱ አስተዋፅኦ እያደረጉ ነው።

በተጨማሪም የሲቪል ማኅበራት እና የሚዲያ ተቋማት የምክክሩን ግልጽነት፣ ገለልተኝነት እና ተዓማኒነት ለማጠናከር ጉልህ ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ከታች ወደ ላይ በተዘረጋ አካታች አሠራር ዜጎች በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በንቃት እንዲሳተፉ ዕድል በመፍጠር የምክክራዊ ዴሞክራሲ መርሆዎችን በተግባር ለማስፈጸም የሚደረግ ጥረት መሆኑን ያሳያል።

ይህን በሰከነ ውይይት፣ በአካታችነት እና በምክንያታዊ መግባባት ላይ የተመሰረተ ባህል ማጠናከር ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም፣ ሀገራዊ መግባባት እና የዴሞክራሲ ግንባታ ጠቃሚ መሠረት ይሆናል።

በኢንቲሃድ አብራር

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: