Search

የሀገራዊ ምክክሩ ጉባኤ ተሳታፊ አዲስ ተወለደው ልጇን "ኮሚሽን" ብላ ሰየመች

ሓሙስ ሐምሌ 16, 2018 142

በአዲስ አበባ ከተማ እየተካሄደ ባለው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ላይ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ወክላ በመሳተፍ ላይ የምትገኘው / ሀዳ አልማህዲ ወንድ ልጅ በሰላም ተገላግላ ለልጇ "ኮሚሽን" የሚል ስም አውጥታለች።

ባለፈው ሳምንት በዚሁ ጉባኤ ላይ ስትሳተፍ የነበረችው የጋምቤላ ክልል ተወካይ / ክርኑዶ ኡጁሉ ወንድ ልጅ በሰላም ተገላግላ ስሙን "ምክክር" ማለቷ የሚታወስ ሲሆን፣ የዘንድሮው ሀገራዊ ምክክር ሂደት እንዲህ ባሉ ድርብ ታሪካዊ እና አስደሳች ክስተቶች ታጅቧል።

ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ኡራ ወረዳ የመጣችው / ሀዳ የመውለጃ ጊዜዋ መድረሱን አስቀድማ ብታውቅም ለኢትዮጵያውያን አብሮነት እና ለሀገራችን ዘላቂ ሰላም በጋራ በሚመከርበት በዚህ ወሳኝ ጉባኤ ላይ መሳተፍ አለብኝ በሚል ጽኑ አቋም መገኘቷን ተናግራለች።

በቆይታዋም በጉባኤው አጀንዳዎች ላይ ለሀገር ይበጃል ያለችውን ሀሳብ በማካፈል ንቁ ተሳትፎ ስታደርግ ቆይታለች።

ይህችው እናት አዲስ አበባ በሚገኘው ኤካ ኮተቤ ሆስፒታል በሰላም ከተገላገለች በኋላ በሰጠችው አስተያየት በዚህ ታሪካዊ ወቅት ልጇን በመውለዷ እጅግ መደሰቷን ገልጻለች።

አዲስ ለተወለደው ልጇም "ኮሚሽን" የሚል ስም ያወጣችለት ሲሆን፤ በቀጣይም የምክክር ተሳትፎዋን አጠናክራ እንደምትቀጥል አረጋግጣለች።

/ ሀዳ አክላም ይህ ሀገራዊ ምክክር የህዝባችን አንድነት የሚጠናከርበት እና ሀገራችንን ወደ አዲስ ብሩህ ምዕራፍ የሚያሻግር እንደሚሆን ጽኑ እምነት እንዳላት ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: