Search

በግዳጅ ወደ ጦርነት፡ የሕገወጡ የህወሓት ቡድን የሞት አዋጅ

ዓርብ ሐምሌ 17, 2018 173

ሕግ የሰው ልጅን ነፃነት ሊያስከብር ሕይወትን ሊጠብቅ እና ፍትህን ሊያሰፍን የሚወጣ የሰለጠነ ማኅበረሰብ መሳሪያ ነው።

ነገር ግን ሕግ ራሱ ሰውን ወደ ሞት ሸለቆ የሚነዳ፣ የመናገር ነፃነትን የሚያፍን እና ሰብአዊነትን የሚያረክስ የጥፋት ዱላ ሲሆንስ?

ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር ጥምረት የፈጠረው፣ የሕዝብን ሀብት በመመዝበር፣ በህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር፣ በኮንትሮባንድ ንግድ እና በዘራፊነት ተደራራቢ ወንጀሎችን በመፈጸም የሚታወቀው ሕገ-ወጡ የህወሓት ቡድን በትግራይ ክልል አውጥቶታል በተባለው አዋጅ ማንነቱን ፍንትው አድርጎ አሳይቷል።

አዋጁ በኢትዮጵያ የሕግ ታሪክ ውስጥ ታይቶም ሆነ ተሰምቶ የማይታወቅ፣ ፍጹም አምባገነንነትን፣ እብሪትን እና ሕገ-ወጥነትን ያነገበ፣ ለትግራይ ሕዝብ የተዘጋጀ የሞት ሰርተፍኬት ነው።

አዋጁ የትግራይን ተወላጅ ለጥቂት ኮንትሮባንዲስቶች እና የፖለቲካ ቁማርተኞች ህልውና ሲባል ብቻ ካልዘመትክ በእስራት እና በሞት ትቀጣለህ የሚል አስፈሪ ድንጋጌን ይዟል።

ለመዋጋት ፈቃደኛ ያልሆነ ማንኛውም የትግራይ ተወላጅ ከ10 ሺህ እስከ 50 ሺህ ብር ይቀጣል። ይህ የገንዘብ ቅጣት ቡድኑ የለመደውን የዘረፋ ባሕሪ ህጋዊ ሽፋን ለመስጠት ያደረገው ሙከራ ነው።

የሞት አዋጁን ሳይፈጽም ቀርቶ ገንዘቡን የተቀጣ ገንዘቡን ከከፈለ በኋላም ቢሆን ወደ ጦር ግንባር እንዲሄድ ይገደዳል። እነዚህን አለመቀበል መጨረሻው የዕድሜ ልክ እስራት እና የሞት ቅጣት ነው።

በ21ኛው ክፍለ ዘመን ሰውን አስገድዶ፣ አስፈራርቶ እና በዛቻ ወደ ጦርነት መንዳት ከዓለም አቀፍ የጦር ወንጀል እና ከሽብርተኝነት በምን ይለያል?

ቡድኑ የራሱን የዘረፋ ኔትዎርክ ለማስቀጠል ሲል ጦርነቱን "ሕዝባዊ" የሚል የውሸት ካባ አልብሶታል። ይሁን እንጂ እውነታው ከዚህ የራቀ ነው። የህወሓት መሪዎች ልጆቻቸውን በምቾት እያኖሩ የድሃውን ልጅ ግን "ጽምዶ" በሚል አስገዳጅ ዘመቻ ወደ እሳት ይማግዳሉ።

ይህን የጥፋት ጥሪ የሚቃወም ደግሞ "ትግራዋይ አይደለም" ተብሎ በመፈረጅ በአደባባይ እርምጃ ይወሰድበታል።

ይህ ቡድን ፖለቲካዊ ድርጅት ሳይሆን የክልሉን ወጣቶች በግዴታ እየመለመለ በጦርነት የሚያስፈጅ፣ ከጦርነቱ ለማምለጥ የሚሞክሩትን ደግሞ በሕገ-ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪነት በሱዳን በቅጥረኝነት እንዲዋጉ አሳልፎ በመሸጥ የደም ገንዘብ የሚሰበስብ አደገኛ ማፊያ መሆኑን በተግባር እያስመሰከረ ነው።

ሕገወጡ የህወሓት ቡድን የሕዝቡን ብሶት ለማፈን ሲል ጦርነቱን የሚተቹ እና ሰላምን የሚሰብኩ ዜጎችን፣ በተለይም በማኅበራዊ ሚዲያ ሀሳባቸውን የሚገልጹትን እስከ 15 ዓመት በሚደርስ እስራት ለመቅጣት ደንግጓል። ይህ ድርጊት የኢትዮጵያን ሕገ-መንግስት እና ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ድንጋጌዎችን በደፈናው የጣሰ ነው።

ዜጎች ሰላምን የመስበክ ሙሉ መብት አላቸው፤ ቡድኑ ግን ክልሉን ወደ አንድ ትልቅ የፖለቲካ እስር ቤት ቀይሮታል።

ከዚህም በላይ የዚህ አዋጅ ሕገ-ወጥነት ጣሪያ የነካው ቡድኑ ራሱን ከኢትዮጵያ የፍትሕ ሥርዓት ውጭ አድርጎ የትግራይ ከፍተኛ ፍርድ ቤትን የመጨረሻው የሰበር ሰሚ ችሎት እንዲሁም ሕገ-ወጡን የክልሉ ምክር ቤት የሕገ-መንግሥት ትርጓሜ ሰጪ አድርጎ መሾሙ ነው።

ዜጎችን ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ማሰር እና መፈተሽ መፍቀዱ ደግሞ ታጣቂዎቹ ያለምንም ጠያቂ የሕዝቡን ንብረት እንዲዘርፉ፣ ወጣቱን አፍሰው በኮንትሮባንድ ንግድ እና በሕገ-ወጥ ሰዎች ዝውውር ለገነቡት የጥፋት ኔትዎርክ ማገዶ እንዲያደርጉት የተሰጠ ፈቃድ ነው።

የሕጉ ተፈጻሚነትም ቢሆን ከጥቅምት 24/2013 ዓ.ም ጀምሮ ወደኋላ ተመልሶ ተግባራዊ ይሆናል ማለቱ የሕግ ወደ ኋላ አለመሥራት መርህን  (The principle of non-retroactivity) የጣሰ እና ቡድኑ ካለፉት ዓመታት ጀምሮ የጠላቸውን እና የተቃወሙትን ሰዎች በሙሉ ለመበቀል የሸረበው ርካሽ ሤራ መሆኑን ያጋልጣል።

የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ይህን የግዳጅ ምልመላ እና የሞት ቅጣት አዋጅ እያወገዙት ይገኛሉ። የፕሪቶሪያው ስምምነት ሙሉ በሙሉ እንዲተገበር፣ ይህ አፋኝ አዋጅ እንዲሰረዝ እና የትግራይ ሕዝብ ከዳግም እልቂት እንዲጠበቅ በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ በቅርቡ  የተካሄደው ሕዝባዊ ሰልፍም የሕዝቡን ትዕግሥት ማለቅ የሚያሳይ ነው።

ሕገወጡ የህወሓት ቡድን  ወታደራዊ አቅሙ ከስሟል። የሕዝብ ድጋፉ ደብዝዟል፤ የውስጥ አንድነቱ ፈርሶ እርስ በእርሱ እየተበላላ ነው። የፖለቲካ ራዕይ ያጣ እና መዋቅሩ የፈረሰበት ይህ ቡድን ዛሬ የቆመው በኮንትሮባንድ፣ ዘረፋ እና በውጭ ኃይሎች ሰው ሰራሽ የመተንፈሻ አካል ላይ ብቻ ነው።

የቡድኑ የሞት አዋጅ እና የዛቻ ፖለቲካ ሞራላዊ እና ቁሳዊ አቅመ-ቢስነቱን የመሸፈኛ ስልት ነው። የትግራይን ሕዝብ እንደ ሸቀጥ እየቸረቸረ በሕገ-ወጥ ሰዎች ዝውውር እና በዘረፋ ህልውናውን ለማቆየት የሚጥረው ይህ የሤራ ቡድን ለኢትዮጵያ  ስጋት ሊሆን አይችልም፤ ይልቅ መጨረሻው የታሪክ ማስተማሪያ እና የውድቀት ማሳያ ሆኖ ያልፋል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: