Search

አካል ጉዳተኞች በሀገራዊ የምክክሩ ፋይዳ ያለው ተሳትፎ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል - ኮሚሽነር ብሌን ገ/መድህን

እሑድ ነሐሴ 11, 2017 97

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን "የአካል ጉዳተኞች ሚና ለውጤታማ ሀገራዊ ምክክር" በሚል መሪ ሀሳብ በአማራ ክልል ከተለያዩ አካባቢዎች ከተውጣጡ አካል ጉዳተኞች ጋር በባህር ዳር ከተማ ውይይት አካሂዷል።

በውይይት መድረኩ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ብሌን ገ/መድህን፤ አካል ጉዳተኞች በሀገራዊ የምክክሩ ከተሳትፎ በዘለለ ፋይዳ ያለው ሃሳብ የሚያፈልቁ የምክክሩ ዋነኛ ባለቤት ናቸው ሲሉ ተናግረዋል።

ኮሚሽኑ የምክክር ሒደቱን አካታችነት ለማረጋገጥ ባለፉት ጊዜያዊት በተለያዩ አካባቢዎች አካል ጉዳተኞችን ለማሳተፍ ጥረት እያደረገ መሆኑን ገልፀዋል።

በዚህም አካል ጉዳተኞች ለሀገር ይጠቅማሉ ያሏቸውን አጀንዳዎች ለምክክር ኮሚሽኑ አስረክበዋል ነው ያሉት።

ቀጣይ በሚደረጉ የሀገራዊ ምክክር መድረኮች የአካል ጉዳተኞች ተሳትፎ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።

አካል ጉዳተኞች በየአካባቢያቸው ሰላምን በመስበክ ልዩነቶችን በምክክር የመፍታት ባህልን ሊያዳብሩ ይገባል ሲሉም አፅንኦት ሰጥተዋል።

ሁላችንም የምክክሩ ባለቤቶች ነን ያሉት ኮሚሽነሯ፤ ሰላሟ የሰፈነ ኢትዮጵያን ለመገንባት ሁላችንም በባለቤትነት ሚናችንን ልንወጣ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው በሀገራዊ የምክክር ሒደቱም ሆነ በዋናው የምክክር መድረክ በንቃት ለመሳተፍ ፍላጎት እንዳላቸው ተናግረዋል።  

ኮሚሽኑ በአሁኑ ወቅት በተለያዩ አካባቢዎች የተለያዩ የሚገኙ ዜጎች ለምክክሩ ውጤታማነት ሚናቸውን እንዲወጡ የሚረዳ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን አሳውቋል።

 

በሳሙኤል ወርቅአየሁ

  

አዳዲስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የኢቢሲን መተግበሪያ ከአፕ ስቶር እና ፕለይ ስቶር አውርደው ዲጂታል ኢቢሲን ይቀላቀሉ።

 

አንድሮይድ (Android) ስልክ የምትጠቀሙ በዚህ ሊንክ https://shorturl.at/6KegY

 

አይኦኤስ (iOS) ስልክ የምትጠቀሙ ደግሞ በዚህ ሊንክ https://shorturl.at/hFuA1