ኢትዮጵያ በታሪኳ ያጋጠሟትን ውስብስብ የፖለቲካ፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ውጣ ውረዶችን በዘላቂነት ለመፍታት እና ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠር ሀገራዊ ምክክር እንደ ዋነኛ አማራጭ መንገድ ሆኖ መጥቷል።
ሀገራችን እነዚህን ፈተናዎች ተሻግራ ወደተሻለ የዕድገት እና የብልፅግና ደረጃ ለመሸጋገር የምታደርገው ሀገራዊ ጥረት ፍሬ ሊያፈራ የሚችለው ዘላቂ ሰላም ሲረጋገጥ ብቻ ነው፡፡
ላለፉት በርካታ ዓመታት ልዩነቶችን በኃይል እና በግጭት ለመፍታት የተሄደባቸው መንገዶች ከውድመት፣ ከእርስ በእርስ ክፍፍል እና ከማኅበራዊ ስብራት ውጭ ያመጡት ዘላቂ መፍትሔ አልነበረም። ታሪክ እንደሚያስተምረው በኃይል የሚጫኑ መፍትሔዎች ጊዜያዊ እፎይታን ከመስጠት ባለፈ የችግሮችን መሠረት አይነቅሉም፡፡
ሕዝቡ ለዘመናት የከፈለውን አላስፈላጊ መስዋዕትነት እና የደረሰውን ሀገራዊ ውድመት መግታት የሚቻለው ከትናንት ታሪካዊ ስህተቶች በመማር፣ አካታች ውይይቶችን በማድረግ እና የእርስ በእርስ መደማመጥ ባህልን በማሳደግ ነው።
ይህንን ታሪካዊ ስህተት ለማረም እና የሀገራችንን የቀጣይ ጉዞ አቅጣጫ በጋራ ለመወሰን የተያዘው ሀገራዊ ምክክር በጠረጴዛ ዙሪያ መቀመጥ ብቻ ሳይሆን፣ ልዩነቶችን በበሰለ መንገድ ማስተናገድ ፍትሃዊ እና አካታች መድረክ መፍጠር እንዲሁም ለቀጣይ ትውልድ የምታልፍ ሰላማዊ እና የተረጋጋች ኢትዮጵያን በጋራ ለመገንባት ያለመ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡
በመሆኑም ውይይት፣ ድርድር እና መደማመጥን ማስቀደም ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ ብቸኛው አማራጭ ሲሆን፣ የዚህ ሀገራዊ ምክክር ስኬት የሚረጋገጠውም የሁሉም ዜጋ፣ የፖለቲካ ኃይሎች እና የማኅበረሰብ ክፍሎች ንቁ እና ቅንነት የተሞላበትን ተሳትፎ ማድረግ ሲችሉ ነው።
በኢንቲሃድ አብራር
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: