Search

የግብፅ ከንቱ ሩጫ እና የማይሰበረው የኢትዮጵያ የሰላም ልዕልና

ዓርብ ሐምሌ 17, 2018 77

ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በኢትዮጵያውያን ብርቱ ትብብር እና ጽናት ማሰናከል ያቃታት ግብፅ፣ አሁን ደግሞ በሌላ አዲስ የከበባ ቁማር ብቅ ብላለች።

ኢትዮጵያ ከ130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ይዛ ከታሪካዊው የቀይ ባሕር መብቷ መገለሏ አግባብ አለመሆኑን በማንሳት ፍትሐዊ የባሕር በር ጥያቄ ስታቀርብ ግብፅ በእጅጉ ተደናግጣለች።

ይህንን ተከትሎም "የቀይ ባሕር ደኅንነት የባሕር ጠረፍ ሀገራት ብቸኛ ኃላፊነት ነው" በሚል ሌላ የከሰረ የዲፕሎማሲ ትብታብ ከጀመረች ሰነባብቷል።

ቀደም ሲል በኢትዮጵያ ዙሪያ ላሉ ሀገራት የውሸት ወዳጅነት በማሳየት ልትተገብረው ያሰበችው የከበባ ፖሊሲ ሙሉ በሙሉ ሲከሽፍባት፣ አሁን ደግሞ በቀጥታ የመተንኮስም ሆነ የመዳፈር ወኔ ስለሌላት ከሶማሊያ ጋር የጋራ መከላከያ ስምምነት በሚል ሽፋን መጠነ ሰፊ የጦር መሳሪያ በማጓጓዝ እጅ አዙር ሤራዋን ሞክራ ብዙ አላዋጣትም።

የሴራ እናት የሆነችው ግብፅ ወዳጅነቷ ከራስ ወዳድነት እና ከጥቅመኝነት የመነጨ እንጂ ከልብ አለመሆኑን በሱዳን በሚገባ አይተናል። ግብፅ ሱዳንን የምታያት የራሷን የውኃ ፖለቲካ ማስፈጸሚያ እና የጥቅሟ ማስጠበቂያ የጓሮ በር አድርጋ እንጂ ለሱዳን ሕዝብ ሰላም እና ብልጽግና ተጨንቃ አታውቅም።

ሱዳን ዛሬ ለገባችበት አሳዛኝ የእርስ በርስ ጦርነት እና የሕዝብ መፈናቀል የግብፅ ጣልቃ ገብነት የራሱን አሉታዊ ሚና ተጫውቷል። ለግብፅ ከራሷ ብሔራዊ ጥቅም ውጭ የሱዳን ሕዝብ ሰቆቃ ምንም ትርጉም አይሰጣትም።

በአንጻሩ ኢትዮጵያ "ለጎረቤት ቅድሚያ" በሚሰጠው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲዋ ሱዳናውያን የራሳቸውን ችግር በራሳቸው እንዲፈቱ እና የውጭ ጣልቃ ገብነት እንዲቆም ከፍተኛ ጥረት ከማድረጓም በላይ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ስደተኞችን ተቀብላ እንደ ሁለተኛ ቤታቸው ማስተናገዷ እውነተኛ ወዳጅነቷን በተግባር ያሳየ ነው።

ኢትዮጵያ የአፍሪካን ሰላም እንደ ራሷ ሰላም የምትቆጥር የፓን-አፍሪካኒዝም ተምሳሌት ናት። ለአፍሪካ ሰላም ስትልም በሩዋንዳ፣ በላይቤሪያ፣ በብሩንዲ፣ እንዲሁም በሱዳኗ አብዬ ግዛት የሰላም አስከባሪ ኃይሎቿን በማሰማራት ውድ የሕይወት መስዋዕትነትን ጭምር ከፍላለች።

በሶማሊያም ቢሆን እውነታው ከዚህ የተለየ አይደለም። ኢትዮጵያ ለሶማሊያ ዝም ብላ ጎረቤት አይደለችም፤ የሁለቱ ሀገራት ሕዝቦች ጥልቅ የባህል፣ የሃይማኖት እና የደም ትስስር አላቸው። ላለፉት 20 ዓመታት ኢትዮጵያ ለሶማሊያ ሰላም እና ፀጥታ አሸባሪውን አልሸባብን በመዋጋት የራሷን ልጆች ደም ገብራለች።

ግብፅ ግን በአዲሱ የአፍሪካ ሕብረት ተልዕኮ (AUSSOM) ሽፋን ወታደሮቿን ከኢትዮጵያ ድንበር አቅራቢያ ለማሰማራት ስትሞክር፣ ከዚህም አልፎ በርካታ የጦር መሣሪያዎችን ወደ ሶማሊያ በማጓጓዝ በአሸባሪዎች እጅ እንዲገቡ በማድረግ ለቀጣናው ሰላም መናጋት ትልቁን ሚና እየተጫወተች ነው።

ይህ ሁሉ ሩጫ ሶማሊያን ለማረጋጋት ሳይሆን፣ የኢትዮጵያን ልማት ለማስተጓጎል እና የከሸፈ የከበባ ፖሊሲዋን በሌላ መንገድ ለመሞከር ነው። ሆኖም የሶማሊያ ሕዝብ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ያለው እጣ ፈንታ የተጋመደ መሆኑን ጠንቅቆ ስለሚያውቅ የግብፅ ጊዜያዊ የጥፋት ሩጫ ብዙም አላራመዳትም።

ኢትዮጵያ ይህን ሁሉ ትዕግሥት እና ጥረት የምታደርገው የጎረቤቷ ሰላም የራሷ ሰላም መሆኑን ጠንቅቃ ስለምታውቅ ነው። የቀጣናው ሀብት በትብብር ከለማ ሕዝብን ከድህነት ማውጣት እና በጋራ ማደግ እንደሚቻል በጽኑ ታምናለች።

ኢትዮጵያ የውኃ ሀብቷን ስትጠቀምም ሆነ የባሕር በርን ስትጠይቅ ማንንም ለመጉዳት ሳይሆን የጋራ ተጠቃሚነትን ማስፈን መሆኑን በሕዳሴ በተግባር አረጋግጣለች።

የራሷን ብቻ የምትጠይቀው እና ፍትሃዊነትን የምታስቀድመው ኢትዮጵያ በዓባይ ላይ የተቀዳጀችው የሃይድሮ-ፖለቲካ ድል በጂኦ-ፖለቲካዊ እና በኢኮኖሚያዊ ልዕልና መድገሟ የማይቀር ነው።

የዘመናት የግብፅ ሴራ ሊከሽፍ የሚችለው ግን መንግሥት እና ሕዝብ በታላቁ ሕዳሴ ግድብ እንዳደረጉት በብሔራዊ ጥቅማቸው ላይ የጸና አቋም ይዘው ለሉዓላዊነታቸው በጋራ ሲቆሙ መሆኑን ታሪክ ዛሬም በድጋሚ እያስታወሰን ይገኛል።

የዓባይ ድል በቀይ ባሕር ላይም የሚደገመው የጠላትን እጅ አዙር ሴራ በመስበር ውስጣዊ አንድነታችንን ስናጠናክር ብቻ ነው!

በለሚ ታደሰ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: