Search

ከውበት ባሻገር፡- የአዲስ አበባ የወንዝ ዳርቻ ልማትና የዜጎች የኑሮ ዘይቤ ለውጥ

ዓርብ ሐምሌ 17, 2018 120

የአፍሪካ መዲና እና የዲፕሎማሲ ማዕከል የሆነችው አዲስ አበባ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ አዲስ ታሪክ እየጻፈች ትገኛለች።

ከተማዋን ለነዋሪዎቿ ምቹ፣ ለጎብኝዎች ደግሞ ማረፊያ ለማድረግ ከተጀመሩት ታላላቅ የልማት እንቅስቃሴዎች መካከል የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል።

ይህ ፕሮጀክት የከተማዋን ገጽታ በመቀየር ረገድ ካስመዘገበው አስደናቂ ውጤት ባሻገር፣ የኅብረተሰቡን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ የኑሮ ደረጃ ከፍ በማድረግ የጎላ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።

ቀደም ሲል የከተማዋ ወንዞችና ዳርቻዎቻቸው የቆሻሻ መጣያ፣ የጽዳት ጉድለት የሚታይባቸው እና ለተለያዩ በሽታዎች መነሻ ነበሩ። የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት ከተጀመረ ወዲህ ግን እነዚህ አካባቢዎች ሙሉ በሙሉ ተለውጠዋል።

በዚህም ቆሻሻ የነበሩ ቦታዎች ወደ ዘመናዊ መዝናኛ ፓርኮች ተቀይረዋል። የወንዞች መበከል እንዲቀንስና የታፈኑ የፍሳሽ መስመሮች እንዲስተካከሉ በማድረግ አዲስ አበባ ንጹሕ አየርና ተፈጥሯዊ ውበት እንድታገኝ አስችሏል።

ፕሮጀክቱ ከተማዋን ውበት ከማጎናጸፍ በላይ የብዙዎችን የዕለት ተዕለት ሕይወት በቀጥታና በተዘዋዋሪ እየቀየረ ይገኛል። ልማት ስንል የሕንፃዎች መገንባት ብቻ ሳይሆን፣ የሰዎች ሕይወትና የኑሮ ደረጃ መለወጥ ነው። የወንዝ ዳርቻ ልማቱም ይህንኑ በተግባር ያረጋገጠ ሆኗል።

በፕሮጀክቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች፣ ሴቶች እና ሥራ አጥ የኅብረተሰብ ክፍሎች በግንባታ፣ በጥበቃ፣ በጽዳት፣ በኮንስትራክሽን እና በፓርኮች አስተዳደር የሥራ ዕድል አግኝተዋል።

በፓርኮቹ አካባቢ የሚገኙ ካፌዎች፣ የዕደ-ጥበብ መደብሮች፣ የፎቶግራፍ እና የቱሪዝም አገልግሎቶች የነዋሪዎችን ገቢ በእጅጉ አሳድገዋል።

ነዋሪዎች ከሥራ ውጥረት አረፍ የሚሉባቸው፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የሚያደርጉባቸው እና ከቤተሰብ ጋር ጥራት ያለውን ጊዜ የሚያሳልፉባቸው አስተማማኝ ስፍራዎችም ተፈጥረዋል።

የአዲስ አበባ ወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት ከተማዋን ለነዋሪዎቿ ጤናማና ምቹ፣ ለኢንቨስትመንትና ለቱሪዝም ደግሞ ተወዳዳሪ የሚያደርጋት የረጅም ጊዜ አርቆ አሳቢነት ውጤት ነው። ፕሮጀክቱ ከተማዋን ከድህነት እና ከብክለት ገጽታ አውጥቶ ወደ ዘመናዊነትና ብልፅግና የምታደርገውን ጉዞ ያፋጠነ የለውጥ ማሳያ ነው።

የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት የአዲስ አበባን የተፈጥሮ ሀብት ከጥፋት አድኖ ወደ ታላቅ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ሀብትነት የለወጠ ስኬታማ ሥራ ነው። ይህ ልማት የከተማዋን ገጽታ ከመገንባት አልፎ የዜጎችን የኑሮ ደረጃ ከፍ በማድረግ የአዲስ አበባን አዲስ ምዕራፍ እያበሰረ ይገኛል።

በአድማሱ አራጋው

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: