Search

ለዘመናት ለተንከባለሉ ሀገራዊ ጥያቄዎች ታሪካዊው የመፍትሔ በረንዳ፤ የዲያስፖራው ድምፅ በሀገራዊ ምክክሩ

ዓርብ ሐምሌ 17, 2018 89

በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በሀገራቸው ሰላምና ደህንነት፣ ሰብዓዊ መብቶች፣ አካታች የፖለቲካ ምህዳር፣ መልካም አስተዳደር እንዲሁም በኢኮኖሚ ፖሊሲዎች ዙሪያ የሚያነሷቸው መሠረታዊ ጥያቄዎች እና የሚያደርጓቸው ሰፊ ውይይቶች አሏቸው።

እነዚህን ጥያቄዎች በሰለጠነ መንገድ ለመፍታት ሀገራዊ ምክክሩ ታሪካዊ አጋጣሚ መሆኑን በውይይቱ ላይ የተወከሉ የዲያስፖራ አባላት ከኢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ ገልጸዋል።

ተወካዮቹ በምክክር ሒደቱ ተቀራርቦ ለመነጋገር የተፈጠረውን ከፍተኛ ዕድልም አድንቀዋል።

ከአሜሪካ የመጡት ተመካካሪ አቶ ማርቆስ አደም እንዳብራሩት፣ ዲያስፖራው በአስተዳደርና የፖለቲካ ምህዳር ሁኔታዎች ላይ በጥልቀት በመመካከር፤ ኢትዮጵያውያን ከጫፍ እስከ ጫፍ በስምምነት ሀገራቸውን እንዲያለሙና በሰላም እንዲኖሩ ይህ መድረክ የጎላ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።

በተመሳሳይ ከስዊድን የመጡት ተመካካሪ መቅደስ ወርቁ በበኩላቸው፣ በምክክሩ ወቅት የተነሱት አብዛኞቹ ጥያቄዎች ለዓመታት ሲንከባለሉ የመጡ መሆናቸውን ጠቁመው፤ በዚሁ ታሪካዊ የምክክር መድረክ አማካኝነት ለእነዚህ ጥያቄዎች ተገቢው ምላሽ ተሰጥቶ የሀገራችንን ልማትና ዕድገት ለማፋጠን ጥሩ አጋጣሚ መፈጠሩን አስረድተዋል።

የምክክር ሒደቱ ኢትዮጵያውያን ተወያይተው በሰለጠነ መንገድ ለችግሮቻቸው ዘላቂ መፍትሔዎችን የሚያገኙበት ሁነኛ መንገድ መሆኑን የገለጹት ደግሞ ከአሜሪካ የመጡት ተመካካሪ ዶክተር ቴዎድሮስ አዳነ ናቸው።

ዶክተር ቴዎድሮስ አክለውም፣ ለልዩነቶች መነሻ የሚሆኑ አጀንዳዎችን በግልጽ ወደ ውይይት ጠረጴዛ ማምጣት ዘላቂ ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠር እጅግ አስፈላጊ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።

በንፍታሌም እንግዳወርቅ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: