የሀገራት ጥንታዊ ታሪክ ሲሰነድ አንዳንዱ በብራና፣ ሌላው በድንጋይ ላይ ሊቀረጽ ይችላል። የኢትዮጵያ የቅርብ ዓመታት የለውጥ ጉዞ ግን በማይጠፋና በማይደበዝዝ የወርቅ ብዕር የተጻፈ ደማቅ ታሪክ ነው። ይህ ጉዞ ለዘመናት ሲንከባለል የመጣው የትውልዶች የኋላቀርነት ዕዳ የተወራረደበት እንዲሁም ለነገው ትውልድ "ዕዳን ሳይሆን ምንዳን" በሚያኖር የጽናት መሠረት የተገነባ አስደናቂ ምዕራፍ ነው።
የትናንቱን ስብራት አክሞ፣ የዛሬን ፈተና ተቋቁሞ፣ የነገውን ብልጽግና በወርቃማ ቀለም የከተበው ይህ የለውጥ ጉዞ፣ በብዙ መመዘኛዎች አዳዲስ ታሪኮች የተፈጸሙበት ልዩ አውድ ነው።
በዓለማችን ላይ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት አስመዘገቡ የሚባሉ በርካታ ሀገራት እንኳ፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማሳካት የተሳናቸውን ተአምራዊ ስኬት፣ ኢትዮጵያ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ዕውን አድርጋለች። ለዚህም ግንባር ቀደም ማሳያ የሚሆነው በስንዴ ልማት የተመዘገበው አንጸባራቂ ድል ነው።
ሀገራችን ለዘመናት በስንዴ ተረጂነትና በልመና ስትታወቅ የቆየች ብትሆንም፣ ዛሬ ላይ ይህን የተመጽዋችነት ታሪክ ቀልብሳ በአጭር ጊዜ ውስጥ ፍላጎቷን በሀገር ውስጥ ምርት መሸፈን ችላለች። ከዚህም አልፎ ወደ ውጭ ገበያ ስንዴ ላኪነት መሸጋገሯ በዓለም አቀፍ ደረጃ አቻ የማይገኝለት ታሪካዊ ክስተት ነው።
ታላላቅ የኢኮኖሚ ተአምር ፈጠሩ የሚባሉ ሀገራት የምግብ ዋስትናቸውን ለማረጋገጥ አሥርተ ዓመታት ሲፈጅባቸው፣ ኢትዮጵያ ግን በአቋራጭ የምግብ ሉዓላዊነት ማማ ላይ መድረሷ የእውነተኛ አርበኝነት ማሳያ ነው።
የወርቅ ብዕሩ ታሪክ በግብርናው ብቻ አላበቃም። በማዕድን ዘርፍ፣ በተለይም በወርቅ ምርትና ወጪ ንግድ የተመዘገበው እመርታ የዚሁ ስኬት ሌላኛው ገጽታ ነው። ቀደም ሲል በኮንትሮባንድ ይባክንና ለጥቂቶች ጥቅም ይውል የነበረውን ማዕድን ወደ ህጋዊ ሥርዓት በማስገባት፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ የወርቅ ወጪ ንግድን በበርካታ እጥፍ ማሳደግ ተችሏል።
ይህ ስኬት ሀብቷን የማታውቅና የምትበዘበዝ ሀገር የሚለውን የትናንት ትርክት ሰብሮ፣ የሀገራችን የውጭ ምንዛሪ ግኝት ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋገረና በወርቅ ላይ የተጻፈ ተጨባጭ ታሪክ ነው።
በተመሳሳይ፣ በቱሪዝሙ ዘርፍ አዳዲስና ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ የቱሪስት መዳረሻዎችን በመገንባት የተሠራው ሥራ የኢትዮጵያን የተፈጥሮ ውበትና የታሪክ ገጸ በረከት ለዓለም አደባባይ አውጥቷል።
የገበታ እና የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶች ከተሞቻችንን ማራኪ በማድረግ የቱሪስቶችን ፍሰት በከፍተኛ ሁኔታ አሳድገዋል። እነዚህ ዘርፈ ብዙ ስኬቶች ሲመዘኑ፣ ዓለምን ያስደመሙ ታላላቅ ሀገራት እንኳ በአንድ ጊዜ በተለያዩ ግንባሮች እንዲህ ያለ የተቀናጀ ድል ለማምጣት ተቸግረዋል።
ኢትዮጵያ ግን ውስብስብ ፈተናዎችን እየተጋፈጠች፣ ተአምራዊ በሚመስል መልኩ ይህንን በማሳካት ዜጎቿን በኩራት የምትመግብና ተስፋቸው የላቀ ትውልድ የምትፈጥር ሀገር መሆኗን አረጋግጣለች። ይህ ድንቅ ታሪክ ማንም ሊሽረው የማይችል፣ በወርቅ ብዕር የታተመ የኢትዮጵያ የልዕልና ማረጋገጫ ነው።
በአዶኒያስ ወልደአረጋይ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: