"ያለችን ሀገር ይህቺው አንዲቷ ኢትዮጵያ ብቻ ናት፤ በመሆኑም ከሕመሟ አውጥተን ወደ ተረጋጋ ሰላምና ፖለቲካ ልናመጣት ይገባል" ሲሉ በሀገራዊ የምክክር መድረኩ ላይ የተገኙ ተመካካሪዎች ጥሪያቸውን አስተላለፉ።
እየተካሄደ ያለው ሀገራዊ የምክክር መድረክ የሃይማኖት አባቶችን፣ አባገዳዎችን፣ የፖለቲካ አመራሮችን እና የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በአንድ ጠረጴዛ ዙሪያ ያገናኘ ታሪካዊ እና እንደዋዛ የማይገኝ ወርቃማ ዕድል መሆኑንም ገልጸዋል።
መድረኩ ዜጎች ስለ ሀገራቸው ችግር፣ ሰላምና ፍቅር በግልጽ እንዲወያዩ ሰፊ መንገድ የከፈተ ከመሆኑም በላይ፤ በቤተሰብ ደረጃ እንኳ ሳይቀር ሊተገበር የሚችል ትልቅ የምክክር ባህልና ትምህርት የተገኘበት መሆኑን አስረድተዋል።
ተመካካሪዎቹ አክለውም፣ በመድረኩ ላይ የሚነሱ መልካም ሐሳቦችና ቁምነገሮች በቃል ብቻ የሚቀሩ መሆን እንደሌለባቸው አሳስበዋል።
ይልቁንም ኢትዮጵያን አሁን ካለችበት ፈተና አውጥቶ ዘላቂ ሰላምና የተረጋጋ የፖለቲካ ምኅዳር ለማስፈን፣ የሚደረጉ ውይይቶችን በፍጥነት ወደ ተግባር መለወጥ እንደሚገባ በአጽንኦት ተናግረዋል።
በምክክሩ ሂደት ውስጥ የሚነሱ የሐሳብ ልዩነቶችን ወደ ግጭት ሳይወስዱ በሰላማዊ መንገድ፣ በመቻቻልና በቀናነት መፍታት መቻሉ የሂደቱ ዋነኛ ስኬትና ቁልፍ ጉዳይ መሆኑም ተጠቅሷል።
እያንዳንዱ የማኅበረሰብ ክፍል የምክክር መድረኩን ሀገራዊ ዓላማ በሚገባ በመረዳቱ፣ በአሁኑ ወቅት ውይይቱ እጅግ በመልካም ሁኔታ እና ዘላቂ ሀገራዊ ስምምነት ላይ በሚያደርስ መንገድ እየተካሄደ እንደሚገኝ ተመካካሪዎቹ አረጋግጠዋል።
በኢንቲሃድ አብራር
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: