ባለፉት ሰባት ዓመታት የኢትዮጵያ ጉዞ በታሪክ ሚዛን ሲለካ፣ ከምንም በላይ ደምቆ የሚታየው በከባድ ማዕበል ውስጥ ሳይሰበሩ ህልው ሆኖ የመቀጠልና ፈተናን ወደ ስኬት የመቀየር ጥልቅ ጥበብ ነው።
የትኛውም ሀገር ቢሆን እንደ ኢትዮጵያ ጦርነትና የውስጥ ግጭቶች፣ የኮቪድ-19 ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ፣ የተፈጥሮ አደጋዎች፣ እንዲሁም እጅግ ከባድና ተደራራቢ የሆኑ የዲፕሎማሲ ጫናዎች በአንድ ጊዜ ሲዘንቡበት፣ በቀላሉ ሊፈርስና ሀገረ-አልባ (Failed State) ወደ መሆን ሊያመራ ይችል ነበር።
ይሁን እንጂ ሀገራችን እነዚህን አስፈሪና ሀገር አፍራሽ ፈተናዎች በተሰበረ ልብ ሳይሆን፣ በማይናወጥ ጽናት፣ በስትራቴጂካዊ ትዕግስትና በረቀቀ የመሪነት ጥበብ ተሻግራቸዋለች።
ይህ ሀገራዊ ጥበብ ከፈታኝ ሁኔታዎች ውስጥ እጅግ ውድ የሆኑ እንቁዎችን የማውጣት፣ እንዲሁም ፈተናን የዕድገትና የብልጽግና መሰላል የማድረግ የላቀ ብቃት ነው። ለዚህ ደግሞ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ያሳየው አስደናቂ የመላመድ አቅም ግንባር ቀደም ማሳያ ነው።
መላው ዓለም በኮሮና ወረርሽኝ ተደናግጦ፣ ዓለም አቀፍ በረራዎች ሙሉ በሙሉ ታግደው በርካታ የዓለም አየር መንገዶች ለከፍተኛ ኪሳራና ለመዘጋት በተዳረጉበት በዚያ የጨለማ ወቅት፣ ብሔራዊ ኩራታችን የሆነው አየር መንገዳችን በፍጥነት ስትራቴጂውን በመቀየር ወደ ካርጎ አገልግሎት ተሸጋገረ።
ይህ እርምጃ ዓለም አቀፍ ቀውስን ወደ ኢኮኖሚያዊ ትርፋማነት በመቀየር፣ አየር መንገዱን መታደግ ብቻ ሳይሆን ለሀገሪቱም ተጨማሪ የውጭ ምንዛሬና ምንዳ ይዞ መምጣት ያስቻለ ታሪካዊ ክስተት ነበር።
ይህ ዓይነቱ እርምጃ የላቀ የአመራር ጥበብንና በችግር ውስጥ ዕድልን የማየት ራዕይን ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው። የኢትዮጵያ ህልውና የተረጋገጠው ችግሮችን በመሸሽ ሳይሆን፣ ፊት ለፊት በመጋፈጥና እያንዳንዱን እንቅፋት ወደ መልካም አጋጣሚ በመለወጥ ነው።
ጫናዎችንና ዲፕሎማሲያዊ ማዕበሎችን እንደ ብረት ማጠንከሪያ በመጠቀም፣ ከውድቀት አፋፍ ተነስታ ወደ ሁለንተናዊ ብልጽግና የምታደርገው ጉዞ ለበርካታ ሀገራት አስተማሪና ሕያው አብነት የሚሆን ነው።
በአጠቃላይ፣ ይህ በፈተና ውስጥ ህልው የመሆን ጥበብ፣ ሀገራችንን ከተጻፈባት የውድቀት ትርክት አውጥቶ ወደ አዲስ የልዕልና ምዕራፍ አሸጋግሯታል።
በረቀቀ፣ አርቆ አሳቢና ፈጣን ውሳኔ ሰጪ አመራር የታገዘው የሀገራችን ጉዞ፣ የፈተናን ጊዜ ወደ ብልጽግና ስምሪት በመቀየር ዓለምን ያስደመመ አዲስ ታሪክ ጽፏል። ኢትዮጵያ በገጠሟት ተግዳሮቶች ግዝፈት ሳይሆን፣ በተገበራቻቸው የስትራቴጂና የመሪነት ጥበቦች ልክ ክንፏን ዘርግታ ከፍታዋን እያረጋገጠች ትገኛለች።
በአዶኒያስ ወልደአረጋይ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: