አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) ጥቅም ላይ የዋለበት ሀገራዊ የምክክር ሂደት፣ ውይይቱ ፍፁም አካታች እና ውጤታማ እንዲሆን በማድረግ የኢትዮጵያን ብሩህ ዕድል፣ ሰላም እና ዘላቂ አንድነት የሚያረጋግጥ ታሪካዊ አጋጣሚ መሆኑን ተሳታፊዎች ተናገሩ።
በምክክሩ ወቅት ዘመናዊ የ AI መለያ ቁጥር አሠራርን ጥቅም ላይ በማዋል፣ ከአራት ሺህ በላይ የነበሩ ተሳታፊዎችን በደረጃ ከአምስት መቶ ወደ አስር አባላት ባሏቸው ቡድኖች በማደራጀት ጥልቅ ምክክር እንዲያደርጉ አስችሏል።
ቴክኖሎጂው ሂደቱን የደገፈበት ይህ አሠራር በሀገራችን ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በተጠናከረ እና በሰፊ ዝግጅት የተካሄደ መሆኑም ተጠቅሷል።
በመድረኩ የተዘረጉትን ስምንት ዋና ዋና አጀንዳዎች መነሻ በማድረግ፣ ማንኛውም ተሳታፊ የሀገራችንን ችግሮች የመለየት፣ ሐሳብ የማስቀመጥ እና የመፍትሔ ስልቶችን የመቀየስ ሰፊ ዕድል አግኝቷል።
በውይይቱም የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በነፃነት እና በመከባበር ሐሳባቸውን መግለጽ ያስቻላቸው ሲሆን፣ የምክክር መድረኩ ዜጎች እርስ በርስ የመደጋገፍ እና የሰውን ችግር እንደራስ አድርጎ የመረዳት ባህልን ያጎለበተ እንደሆነ ተሳታፊዎች አስረድተዋል።
ይህ ዘመናዊ አካሄድ ኢትዮጵያን ወደተሻለ የሰላምና የአንድነት ደረጃ የሚያሸጋግር፣ እንዲሁም በዓለም አቀፍ እና በአፍሪካ ደረጃ ተወዳዳሪ የሚያደርግ አሠራር እንደሆነ ተጠቁሟል።
ባለፉት ዓመታት እንደ አድዋ ድል ያሉ ታሪካዊ አጋጣሚዎችን መነሻ በማድረግ፣ አሁን ያገኘነውን ታሪካዊ የምክክር አጋጣሚ በመጠቀም ሀገራችን ኢትዮጵያን በአንድ ዓላማ፣ በአንድ አጀንዳ እና በአንድ ዕቅድ ለመገንባት ሁሉም ሊረባረብ እንደሚገባ ተሳታፊዎች ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
በኢንቲሃድ አብራር
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: