Search

በወሳኝ የታሪክ መታጠፊያ ላይ

ዓርብ ሐምሌ 17, 2018 56

የዓለማችንን ታሪክ ስንመረምር፣ ዛሬ ላይ የዕድገትና የስልጣኔ ማማ ላይ የደረሱ ሀገራት ሁሉ የየራሳቸው "ወሳኝ የታሪክ መታጠፊያ" (Historical Turning Point) እንዳላቸው እንገነዘባለን።

እነዚህ ሀገራት ከድህነት አዘቅት ወጥተው ወደ ልዕልና የተሸጋገሩት በአጋጣሚ ሳይሆን፣ ታሪካዊውን የለውጥ ዕድል በአግባቡ በተረዱና ቆራጥ ውሳኔ ባሳለፉ መሪዎቻቸውና ትውልዶቻቸው ጥረት ነው።

ለዚህ ዓይነተኛ ማሳያ የምትሆነው ቻይና ናት። የማኦ ዜዱንግ ዘመን ካበቃ በኋላ፣ ዴንግ ዥያኦፒንግ ወደ ስልጣን ሲመጡ ያካሄዱት የኢኮኖሚ ሪፎርምና "የበር መክፈት" ፖሊሲ ለቻይናውያን የዘመናችን ታላቅ የታሪክ መታጠፊያ ነበር።

ርዕዮተ-ዓለማዊ ግትርነትን ትተው፣ "ድመት አይጥ እስከያዘች ድረስ ጥቁርም ሆነች ነጭ ለውጥ የለውም" በሚል ገቢር ነበብ (Pragmatic) እሳቤ፣ ሀገሪቱን ከተዘጋና ከተዳከመ ኢኮኖሚ ወደ ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ኃያልነት አሸጋገሯት። ይህ ቆራጥ የለውጥ ውሳኔ፣ ቻይናን ዛሬ ላለችበት የቴክኖሎጂ እና የኢንዱስትሪ ልዕልና አብቅቷታል።

ወደ ሀገራችን ስንመጣ፣ ኢትዮጵያ ረጅም የሀገረ መንግሥት ታሪክ ያላት ብትሆንም፣ በየዘመናቱ ያጋጠሟትን በርካታ የታሪክ መታጠፊያዎች ሳትጠቀምባቸው አልፋለች። የኢንዱስትሪ አብዮቶችን በሩቁ እያየን፣ የፖለቲካ ስብራትና የመጠፋፋት አዙሪት ወደኋላ ሲጎትተን ኖሯል።

ሆኖም፣ የለውጡ ኃይል ሀገራዊ ኃላፊነትን ከተረከበበት ጊዜ ጀምሮ፣ ኢትዮጵያ የራሷን ትክክለኛ እና ወሳኝ የታሪክ መታጠፊያ ላይ ቆማለች። ይህ የኛ መታጠፊያ፣ የትናንትን ስብራት በመደመር እሳቤ ጠግኖ፣ ዛሬን በልማት አጽንቶ፣ ነገን በብልጽግና የሚያልም ነው።

ልክ ቻይናውያን ርዕዮተ-ዓለማዊ እስረኝነትን እንደሰበሩት ሁሉ፣ እኛም የዘመናት "አለመቻል" ትርክትን ሰብረን ወጥተናል።

በኢኮኖሚው ዘርፍ የተወሰዱት ደፋር የማክሮ-ኢኮኖሚ ማሻሻያዎች፣ ሀገራችንን ከዕዳ ወደ ምንዳ፣ ከተረጂነት ወደ አምራችነት እያሸጋገሯት ነው።

በግብርናው በተለይ በስንዴ ልማት፣ በቴክኖሎጂ፣ በማዕድንና በቱሪዝም ዘርፎች እየተመዘገቡ ያሉት ተአምራዊ ድሎች የዚህ ታሪካዊ ምዕራፍ አኩሪ ፍሬዎች ናቸው።

የተጓተቱና የብክነት ማሳያ የነበሩ ሜጋ ፕሮጀክቶች እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ያሉት ፕሮጀክቶች ተጠናቅቀው ፍሬ ማፍራታቸው፣ የኮሪደር ልማቶች ከተሞቻችንን ወደ ስልጣኔ ማዕከልነት መቀየራቸው እንዲሁም ሀገራችን በብሪክስ አባልነትና በጠንካራ የውሃና የባሕር በር ዲፕሎማሲ ዓለም አቀፍ ተሰሚነቷን ማረጋገጧ፣ መታጠፊያውን በስኬት እየተሻገርነው ለመሆኑ ህያው ምስክሮች ናቸው።

ታላላቅ ሀገራት ከመከራና ከድህነት ተነስተው ዛሬ ላሉበት ከፍታ የበቁት መታጠፊያውን በድፍረትና በብልሃት በማለፋቸው ነው። ኢትዮጵያም ዛሬ ላይ ያጋጠሟትን ዘርፈ ብዙ የውስጥና የውጭ ፈተናዎች ወደ ዕድል በመቀየር፣ ይህንን ወሳኝ የታሪክ መታጠፊያ በብቃት እየተወጣችው ትገኛለች።

ይህ የለውጥ ትውልድ የዘመናችንን ዕድል ተጠቅሞ ጠንካራ፣ የበለጸገችና ልዕልናዋ በዓለም አደባባይ የተረጋገጠ ኢትዮጵያን የመገንባት ታሪካዊ ኃላፊነቱን በተግባር እያረጋገጠ ነው።

በአዶኒያስ ወልደአረጋይ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: