Search

ለነገው ትውልድ የሚሆን ዘመን ተሻጋሪ አረንጓዴ ስጦታ

ዓርብ ሐምሌ 17, 2018 71

ሀገራችን እያካሄደች የሚገኘው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የተራቆቱ መሬቶችን መልሶ ለማልማትና ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ የተጀመረ ታሪካዊና ሀገራዊ ንቅናቄ ነው።

ይህ ንቅናቄ የዛሬውን ማህበረሰብ ፍላጎት እያሟላ ለነገው ትውልድ የተረጋገጠ ህልውና እና የበለፀገች ለምለም ሀገር የማስረከብ ዘመን ተሻጋሪ ራዕይን ያነገበ ሲሆን በአጭር ጊዜ ውስጥም እጅግ አስደናቂ ስኬቶችን ማስመዝገብ ችሏል።

የዚህ ታላቅ ፕሮጀክት ዋና ነዳጅ የኢትዮጵያ ሕዝብ በእድሜ በጾታ በብሔር በሃይማኖትና በፖለቲካ አመለካከት ሳይለያይ ከህፃናት እስከ አዛውንት ከመንግሥት ሰራተኞች እስከ ግል ባለሀብቶች ድረስ በአንድነት በመሰለፍ ያሳየው ሰፊ ተሳትፎና ሀገራዊ ሕብረት ነው።

ኢትዮጵያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎቿን በአንድ ቀን በማስተባበር በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ችግኞችን መትከል እንደሚቻል በተግባር በማሳየት ሌሎች ሀገራት ሕዝባቸውን ለአካባቢ ጥበቃ እንዴት ማነሳሳት እንዳለባቸው ትልቅ ማሳያ ሆናለች።

በትክክለኛ አመራርና በሕዝብ ተነሳሽነት መንግሥትና ሕዝብ ባደረጉት ተከታታይ እንክብካቤም ችግኞቹ በከፍተኛ ሁኔታ በመፅደቃቸው የተራቆቱ ተራራዎች አረንጓዴ ለብሰዋል ምንጮች እንደገና መፍለቅ ጀምረዋል የከርሰ ምድር ውኃ በልፅጓል እንዲሁም የሀገራችን የደን ሽፋን በከፍተኛ ደረጃ አድጓል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንደገለጹት መርሐ ግብሩ ዛፍ የመትከል ሥራ ብቻ ሳይሆን ከአየር ንብረት ጥበቃ ባለፈ በቀጥታ ከኢኮኖሚ ብልፅግና ጋር የተሳሰረ ነው።

ከተተከሉት ችግኞች መካከል እንደ አቮካዶ፣ ማንጎ፣ ፓፓያ፣ እንጆሪ እና ቡና ያሉ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የፍራፍሬና የኢኮኖሚ ተክሎች በመካተታቸው ለአርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች አዲስ የገቢ ምንጭ በመፍጠር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና የዜጎችን ሕይወት ለመለወጥ አዲስ ዕይታን ፈጥሯል።

በሌላ በኩል የአየር ንብረት ለውጥ ድንበር የማይበግረው በመሆኑ ኢትዮጵያ ችግኞችን ለጎረቤት ሀገራት በማጋራት የአየር ንብረት ለውጥን በጋራ ለመከላከል የሚያስችል የቀጣናዊ ትብብርና የአረንጓዴ ዲፕሎማሲ ተሞክሮን በተግባር አስተዋውቃለች።

ይህ ስኬት ትላልቅ የገንዘብ በጀቶችን ብቻ ከመጠበቅ ይልቅ በውስጥ አቅምና በህዝብ አንድነት ትልቅ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ለዓለም ያሳየ በመሆኑ በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ እንደ ትልቅ አርዓያና ተጠቃሽ ተሞክሮ እየቀረበ ይገኛል።

በመሆኑም ይህ ለልጆቻችን የተራቆተች ሳይሆን አረንጓዴ እና ምርታማ ሀገር የማውረስ ትልቅ የትውልድ ፕሮጀክት በመሆኑ እስካሁን የተመዘገቡ ስኬቶችን አጠናክሮ በመቀጠልና እንክብካቤውን ባህል በማድረግ ታሪካዊ ዐሻራችንን ለትውልድ ማኖር ይኖርብናል።

በብሌን ደምበሎ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: