ማምረት ሉዓላዊነትን ያጎናጽፋል የሚለው እሳቤ ብቻ ሳይሆን፣ ኢትዮጵያ ከጥገኝነት ስነ-ልቦና ተላቅቃ የራሷን እጣ ፈንታ በራሷ የመወሰን ብቃትን የምታረጋግጥበት የህልውና መሰረት ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቅርቡ በፓርላማ እንዳነሱት ከለውጡ በፊት የነበረው የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ አቅም እጅግ ደካማ ነበር። ፋብሪካዎቻችን ቢሰሩ እንኳ ከግማሽ በማይበልጥ አቅማቸው እየተንቀራፈፉ፣ በየዓመቱ ለወጪ ንግድ ገቢ ጥቂት መቶ ሚሊዮን ዶላሮችን ብቻ ያበረክቱ ነበር።
እንደ ሀገር ከቡና፣ ከሌሎች የግብርና ምርቶች እንዲሁም በተለይ ከወርቅ ማዕድን ሀብታችን እና ከኢትዮጵያ አየር መንገድ መስተንግዶ ውጪ፣ በኢንዱስትሪዎቻችን እሴት ተጨምሮባቸው ያመረትናቸውን ምርቶች ወደ ውጭ በመላክ ረገድ እምብዛም ነበርን። ይህን አስከፊ ታሪክ ለመቀየር ባለፉት አምስት ዓመታት የተተገበሩት የማክሮ-ኢኮኖሚ ማሻሻያዎች መንግሥት ሀገራችንን ወደ ላቀ የኢኮኖሚ ምዕራፍ ለማሸጋገር ያለውን ቁርጠኝነት በተጨባጭ አሳይተዋል።
የመሠረተ ልማት ዝርጋታ፣ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን እና የግብርና ዘመናዊነት የዚህ ራዕይ አካላት ሲሆኑ፣ በተለይም የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ያስመዘገበው ስኬት የኢኮኖሚው የጀርባ አጥንት መሆኑን አረጋግጧል።
ከለውጥ በፊት ከ47 በመቶ በታች የነበረው የኢንዱስትሪ የማምረት አቅም ዛሬ ወደሚያስገርም 67 በመቶ አድጓል። በዚህም የማምረቻው ዘርፍ ምርት በ24 በመቶ፣ የሲሚንቶ ምርት በ16 በመቶ እንዲሁም የኢንዱስትሪው ዘርፍ በአጠቃላይ በ12.7 በመቶ ዕድገት ማስመዝገብ ችሏል። ቀደም ባሉት አስርት ዓመታት የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ከሀገር ውስጥ የግብርና አቅርቦት ሰንሰለት ጋር ምንም ዓይነት ትስስር ያልነበራቸው፣ ጥሬ ዕቃን ሙሉ በሙሉ ከውጭ በማምጣት ምርትን ወደ ውጭ ለመላክ ብቻ የተዋቀሩ ነበሩ።
ዛሬ ግን ይህ ታሪክ አብቅቶ የኢንዱስትሪ አጥሮቹ ፈርሰዋል። ባለፉት አምስት ዓመታት በተተገበረው የመደመር እሳቤና ፓርኮቹ ወደ ተቀናጀ የኢኮኖሚ ቀጠና በመቀየራቸው፣ ከዚህ ቀደም 5 በመቶ ብቻ የነበረው የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች ድርሻ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከ65 በመቶ በላይ ሊያድግ ችሏል።
ይህ የመዋቅር ሽግግር መንግስት እና የግል ዘርፉን በማስተሳሰር የውጭ ቴክኖሎጂን ወደ ሀገር ውስጥ ካፒታልነት የቀየረ ስትራቴጂካዊ ድል ነው። ከዚህ ጎን ለጎን በሐምሌ 2016 የተደረገው የውጭ ምንዛሬ ተመን ማሻሻያም ፍሬ ማፍራት ጀምሯል። የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (IMF) የ3.4 ቢሊዮን ዶላር ፕሮግራም የታለመለትን ዓላማ እያሳካ ሲሆን፣ ብሄራዊ ባንኩ የዋጋ ንረትን በመቆጣጠር ላይ እያለ የኢትዮጵያ ምርቶች በውጭ ገበያ ይበልጥ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ እያደረገ ይገኛል።
በዚህም ማምረት ለኢትዮጵያ የሉዓላዊነት ማረጋገጫ ብቻ ሳይሆን የፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ሞተርም ጭምር ሆኗል። ዘርፉ ያስመዘገበው የኤክስፖርት ገቢ ዕድገት የማምረት አቅማችን የደረሰበትን ከፍታ በግልፅ ያመላክታል። ለዓመታት ከ3 ቢሊየን ዶላር ያልዘለለው የኤክስፖርት ገቢያችን በአሁኑ ወቅት ወደ 10 ቢሊየን ዶላር መገስገሱ ታላቅ ስኬት ነው።
ይህንን ስኬት በተመለከተ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲያብራሩ፣ "ኢትዮጵያ ባለፉት አሥራ ሰባት ዓመታት ከወጪ ንግድ በአጠቃላይ አሥራ አንድ ቢሊዮን ዶላር አግኝታለች፤ አሁን ያንን የአሥራ ሰባት ዓመት ድምር በአንድ ዓመት ውስጥ አስገኝተናል" ብለዋል። በእርግጥም በአንድ ወቅት የወጪ ንግድ ገቢዋን በአሥርተ ዓመታት ትለካ የነበረች ሀገር አሁን በወራት እየለካችው ነዉ። ለውጡ በትንሽ በትንሹ የሚታይ ሳይሆን በከፍተኛ ፍጥነት የተከሰተ ሆኗል።
መንግስት ማዳበሪያን ጨምሮ መሰረታዊ ምርቶችን በራስ አቅም ማምረት አለመቻል በሀገር እና በህዝብ ላይ የሚያመጣውን የሉዓላዊነት ስጋት በአግባቡ ተገንዝቦ ፖሊሲዎቹን ወደ ሀገር በቀል ኢኮኖሚና አምራችነት አዙሯል። ይህ እርምጃ የውጭ ምንዛሬን አድኖ በሀገር ውስጥ እንዲቀር ከማስቻሉም በላይ አገራችንን ከዓለም አቀፍ የዋጋ መዋዠቅ እና የአቅርቦት ሰንሰለት መስተጓጎል እየታደጋት ነዉ።
ይህ ሁሉ ስኬት ሊመዘገብ የቻለው መንግስት ለሀገር ውስጥም ሆነ ለውጭ ባለሀብቶች ምቹ የኢንቨስትመንት ከባቢ በመፍጠሩ ነው። የታክስ ክፍያ እፎይታ፣ ከውጭ ለሚያስገቧቸው ማሽነሪዎች እና የማምረቻ ግብዓቶች የተደረገ ድጋፍ፣ እንዲሁም ዋስትናን የመሳሰሉ ማበረታቻዎች የሀገር ውስጥ አቅም ለመፍጠር ትልቅ አስተዋጽዖ አድርገዋል።
በአጠቃላይ ኢትዮጵያ አሁን ላይ እየተገበረችው ያለው የኢኮኖሚ ፖሊሲ፣ ወይ ለውጭ ኢንቨስትመንት ተገዥ መሆን አለባት አሊያም ለዓለም ዝግ መሆን አለባት የሚለውን የአረጀ አስተሳሰብ የሰበረ ነው።
የሥራ ዕድል በመፍጠር፣ ከውጪ የሚገቡ ዕቃዎችን በሀገር ውስጥ ምርት በመተካት እና የቴክኖሎጂ ሽግግርን በማምጣት የአምራች ኢንዱስትሪው ለዘላቂ እድገት የበኩሉን አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል። ሀገራችን በአፍሪካ ገበያ ተወዳዳሪ የሚሆን ጠንካራ የኢንዱስትሪ ስርዓተ ምህዳር በመገንባት ላይ መሆኗም፣ የነገዋ ኢትዮጵያ በእራሷ የምትተማመን እና ሉዓላዊነቷን በኢኮኖሚ አቅሟ ያረጋገጠች ሀገር እንደምትሆን ቁልፍ ማሳያ ነው።
በበረከት ሽመልስ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: