ሁለንተናዊ ሀገራዊ ለውጡን መነሻ ያደረገው የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ተቋማዊ ሪፎርም በውጤታማነት መቀጠሉን እና በ2019 በጀት ዓመትም ይህንኑ አጠናክሮ ለማስቀጠል የሚያስችል ስትራቴጂካዊ አቅጣጫ ማስቀመጡን ኮርፖሬሽኑ አስታውቋል።
ኮርፖሬሽኑ የ2018 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም ግምገማ እና የ2019 መሪ ዕቅድ ውይይቱን በቢሾፍቱ ከተማ ለሁለት ቀናት አካሂዷል።
በመድረኩ በበጀት ዓመቱ የተቀመጠውን ዕቅድ 97 በመቶ ማከናወን መቻሉ የተገለፀ ሲሆን፣ በገቢ ዕድገት፣ በቤት ልማት፣ በመስፈጸም አቅም እና በቤት አስተዳደር ረገድ የተከናወኑት ሥራዎች የተቋሙን አጠቃላይ የለውጥ ጉዞ ማረጋገጣቸው ተጠቁሟል።
በተጨማሪም የሕዝብና የመንግስት ጥቅም ለማስጠበቅ በፍርድ ቤት በተከናወኑ ክርክሮች በርካታ ይዞታዎችን ማስመለስ ተችሏል።
ኮርፖሬሽኑ በአፍሪካ ገበያ ለመሰማራት ባለው ራዕይ መሠረት፣ በደቡብ ሱዳን ጁባ ከተማ በቤት ልማት ለመሳተፍ ከደቡብ ሱዳን ኢኳቶሪያል ስቴት ጋር የተደረሰው ስምምነት ወደ ተግባር ለማስገባት ሥራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ።
የልማት ፕሮጀክቶችን በተመለከተ የፒያሳ እና የጎልድ ሳይት ፕሮጀክቶችን አጠናቆ ወደ አገልግሎት ማስገባት የተቻለ ሲሆን፣ ዘመናዊ የ3ዲ የግንባታ ቴክኖሎጂን ለማስፋፋት የሚያስችሉ የመጀመሪያዎቹ የሙከራ ቤቶች ግንባታም በመከናወን ላይ ይገኛሉ።
በሌላ በኩል የቤቶች ቆጠራና የመረጃ ማሰባሰብ ሥራ በመጠናቀቁ ዘመናዊ የቤት አስተዳደር ሥርዓትን ማጠናከር የተቻለ ሲሆን፣ በርካታ የንግድ ቤቶችም ከደንበኞች ጋር በትብብር ተገንብተው ወደ ኪራይ አገልግሎት በመግባታቸው ከፍተኛ ገቢ ማስገኘት ጀምረዋል።
ከዚህ ባሻገር የተቋሙን የ50 ዓመት የጉዞ ታሪክና ስኬቶች የሚያስተዋውቁ የተለያዩ መርሐግብሮች በኢዮቤልዩ በዓሉ ወቅት ለአራት ተከታታይ ቀናት በታላቅ ድምቀት ተከብረዋል፤ በዚህም የተቋሙን ገጽታ መቀየር መቻሉ በስፋት ተገልጿል።
በአዲሱ የ2019 በጀት ዓመት ዘመናዊና ፈጣን የግንባታ ቴክኖሎጂዎችን ሥራ ላይ ማዋል፣ የቤት አቅርቦትን ማሳደግ፣ የገቢ ምንጮችንና የፋይናንስ አማራጮችን ማስፋፋት እንዲሁም የአሰራር አቅምን ማጠናከር ዋነኛ ስትራቴጂካዊ አቅጣጫዎች ሆነው መቀመጣቸውን የኮርፖሬሽኑ መረጃ ያመላክታል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: