የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ተወካይ አቶ ጣሒር ሙሐመድ ከኢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ የሀገራዊ ምክክር መድረኩ በርካታ ጊዜያትን ወስዶ ዝግጅት ሲደረግበት የቆየና ልዩነቶችን ወደ መግባባት በማምጣት የእርስ በእርስ ትስስርን የፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።
አቶ ጣሒር እንዳብራሩት፤ በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍሎች በተለያዩ ጊዜያት አጀንዳዎች እየተነሱ የጋራ መግባባት ላይ ያልተደረሰባቸው በርካታ ጉዳዮች አሉ።
የታሪክንም ሆነ ነባራዊ ሁኔታውን ተጨባጭ ያደረጉ በርካታ የኅብረተሰብ ክፍሎች፣ ከሃይማኖት፣ ከብሔር ብሔረሰብ እንዲሁም ከሙያ ማህበራት ጭምር የመብትና የህልውና የሕግ መዋቅርን የተመለከቱ ጥያቄዎቻቸውንና ችግሮቻቸውን ሊፈቱበት የሚችሉበት መድረክ መሆኑንም አስረድተዋል።
ከ4 ሺህ በላይ ሰዎች በተሳተፉበት በዚህ መድረክ፣ አጀንዳዎች ወደ ውይይት መጥተው ከዝግጅት ባለፈ በቀጥታ ወደ ጉዳዮቹ ገብተው ውይይት ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
በፖለቲካ ሜዳ ላይ ተለያይተንበታል የምንላቸው ጉዳዮች ወደ መድረክ መጥተው ውይይት ሲደረግባቸው፣ ወደ መግባባት የማምጣት፣ የጋራ የማድረግ እንዲሁም ወደ መሐል የመሳብ ዝንባሌዎች ታይተዋል ሲሉም አክለው ገልጸዋል።
አቶ ጣሒር አያይዘውም፤ መድረኩ በፖለቲካው መስክ እስከዛሬ ከተደረጉት ውይይቶችና ክርክሮች ሁሉ ለየት ባለ ሁኔታ የእርስ በእርስ ትስስር እንዲፈጠር ያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።
በተጨማሪም የልዩ ልዩ ህዝቦችን ጥያቄ፣ የመጡበትን ቦታ፣ ባህልና ማንነታቸውን ለማወቅ የረዳ እጅግ ጠቃሚ ሂደት መሆኑን በመጠቆም፣ በሒደቱም የተሻለ ውጤት እንደሚመጣ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
በንፍታሌም እንግዳወርቅ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: