በታሪክ ለዘመናት ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብቶቿን ለልማት ለማዋል በሞከረች ቁጥር ከጂኦፖለቲካዊ ፉክክር፣ ከውጫዊ ጫናዎችና ከተለያዩ የዲፕሎማሲ ፈተናዎች ጋር ተጋፍጣለች።
በተለይ የዓባይ ወንዝ አጠቃቀም፣ የቀይ ባሕር የንግድ መስመሮች እና የቀጣናው የደኅንነት ጉዳዮች የብዙ ሀገራት ፍላጎት የሚገናኙባቸው በመሆናቸው ኢትዮጵያ በአፍሪካ ጂኦፖለቲካ ውስጥ ወሳኝ ቦታ ትይዛለች።
ይሁን እንጂ ለእነዚህ ፈተናዎች የተሰጠው ምላሽ ግጭትን በማስፋፋት ሳይሆን በውይይት፣ በዲፕሎማሲ እና በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ ህልውናን በማጠናከር ነው፤ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብም የዚህ ትልቅ ማሳያ ነው። ግድቡ ውኃን እንደ ግፊት መሣሪያ ሳይሆን እንደ ኃይል ማመንጫ፣ እንደ ኢኮኖሚ ትስስር እና እንደ የቀጣናው የጋራ ብልጽግና መሠረት የሚጠቀምበትን መንገድ አሳይቷል።
የቀይ ባሕር ሰላም፣ የዓባይ ትብብር እና የቀጣናው ኢኮኖሚያዊ ትስስር እርስ በርሳቸው የተያያዙ ናቸው። የተፈጥሮ ሀብቶች የፉክክር ምንጭ ሳይሆኑ የጋራ ብልጽግና መሠረት በሚሆኑበት ጊዜ ዘላቂ ሰላምና ልማት ይገነባል።
ኢትዮጵያ ከተራሮቿ የሚፈልቁ ወንዞች ድንበር ተሻግረው ለበርካታ ሀገራት ሕይወትን፣ ግብርናንና ኢኮኖሚን ያጎለብታሉ። ይህ የተፈጥሮ ሀብት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚን ለማዳከም እንቅልፍ በማይተኙ ኃይሎች ሴራ ቢዘገይም፣ ሀገራችን ግን እንደ ግጭት መሣሪያ ሳይሆን እንደ ትብብር ድልድይ ማየት፣ ፍትሐዊና ምክንያታዊ አጠቃቀምን በማረጋገጥ የጋራ ብልጽግናን መገንባት አማራጭ አድርጋለች።
ኢትዮጵያ የድህነትንና የኋላቀርነትን ሰንሰለት ለመበጣጠስ ከነደፈቻቸው ታሪካዊ ፕሮጀክቶች መካከል ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከመጀመሪያዎቹ አንዱ በመሆኑ ዋና ዓላማው የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት፣ የኢትዮጵያን የኃይል እጥረት መቅረፍ፣ ለጎረቤት ሀገራትም ኃይል በማቅረብ የቀጣናውን ኢኮኖሚያዊ ትስስር ማጠናከር ላይ ነው።
የዚህ ፕሮጀክት ትልቁ ገጽታ ግድቡ ብቻ ሳይሆን ከጀርባው የቆመው የሕዝብ አንድነት ነው። ገበሬው ከእርሻው፣ ተማሪው ከትምህርት ቤቱ፣ ሠራተኛው ከደመወዙ፣ በውጭ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ ከገቢው በማዋጣት አንድ ታሪካዊ ሕልም እውን እንዲሆን አብሮ ቆሟል። ይህ የተባበረ ሕዝብ ኃይል የኢትዮጵያ "የተባበሩ ብርቱ ክንዶች" እውነተኛ ትርጉምን በተግባር አሳይቷል።
የህዳሴ ግድብ ከኃይል ማመንጨት ባሻገር የመስኖ ልማትን ለማስፋፋት፣ የምግብ ዋስትናን ለማጠናከር፣ የውኃ አስተዳደርን ለማዘመን፣ የጎርፍና የድርቅ አደጋዎችን ለመቀነስ፣ የቱሪዝምና የዓሣ ሀብትን ለማሳደግ እንዲሁም የአረንጓዴ ልማትን ለማፋጠን ሰፊ አቅም አለው።
የወደፊቱ ዓለም የውኃ ፉክክር ሳይሆን የውሓ ትብብር የሚለውን መርህ በተግባር ማረጋገጥ ከቻለ፣ ኢትዮጵያ የምታበረክተው አስተዋፅኦ በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃም የሚገነዘብ ይሆናል። የሀገራችን ወንዞች የሚያስተላልፉት መልዕክት "ውኃን እንካፈል፤ ልማትንም እንካፈል" የሚል ነው።
ውኃዎቿ የልመና ምንጭ አይደሉም፤ የትብብር ምንጭ ናቸው። የጣልቃ ገብነት መነሻ ሳይሆኑ የመፍትሔ መሠረት ናቸው። የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብም ይህንን እሳቤ በተግባር የሚያረጋግጥ የትውልድ ፕሮጀክት ነው፤ የኢትዮጵያ የተባበሩ ብርቱ ክንዶች የልማት፣ የሰላም እና የቀጣናዊ ትብብር ተምሳሌት ሆነው ይቀጥላሉ።
በልዩ እሸቱ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: