ኢትዮጵያ ልዩ የቱሪዝም እምቅ አቅሟን በተጨባጭ ለማሳየት እና በአፍሪካውያን መካከል ያለውን የሕዝብ ለሕዝብ ጠንካራ ግንኙነት ይበልጥ ለማሳደግ ያለመ አህጉር አቀፍ የቱሪዝም ማስተዋወቂያ መርሃ ግብር ጀምራለች።
የዚህ ግዙፍ አህጉራዊ ዘመቻ መነሻ በማድረግም በናይሮቢ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ፤ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከቱሪዝም ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ እና ከኩሪፍቱ ሪዞርቶች (ቦስተን ፓርትነርስ) ጋር በመተባበር በኬንያ የሁለት ቀናት የቱሪዝም ማስተዋወቂያ መድረክ አዘጋጅቷል።
በዚህ መድረክ ላይ የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎችን፣ የንግዱ ማኅበረሰብ መሪዎችን፣ የብዙኃን መገናኛ ተወካዮችንና የጉብኝት (ቱር) ኦፕሬተሮችን ጨምሮ በርካታ ታዳሚዎች ተገኝተዋል።
በኬንያ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ባጫ ደበሌ ለተሳታፊዎቹ ባደረጉት ንግግር፣ ኢትዮጵያ የሰው ልጅ መገኛ መሆኗን ገልጸው፤ በዩኔስኮ የተመዘገቡ 18 የዓለም ቅርሶችን ጨምሮ ሀገራችን ያላትን አስደናቂ ታሪካዊና ባህላዊ እሴት በሰፊው አጉልተዋል።
በተጨማሪም ለተሳታፊዎቹ በኢትዮጵያ በፍጥነት እያደገ ስላለው የቱሪዝም ዘርፍና ስለ ዓለም አቀፍ ደረጃ የቱሪስት መዳረሻዎቻችን ሰፊ ማብራሪያ ተሰጥቷል።
የዚሁ አህጉራዊ ማስተዋወቂያ መርሃ ግብር አካል በሆነው ስምምነት መሠረትም፣ በመድረኩ ላይ የተገኙት ታዳሚዎች የኢትዮጵያን አንጸባራቂ የቱሪዝም መስህቦች በአካል ተገኝተው ለመጎብኘት በቀጣይ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚጓዙ ታውቋል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: