Search

ከግጭት ይልቅ በጠረጴዛ ዙሪያ የመቀመጥ ባህል ሲዳብር የነገዋን ኢትዮጵያ በተስፋ የመገንባት ዕድል ይሰፋል፡- መምህር ዳንኤል ሰይፈሚካኤል

ዓርብ ሐምሌ 17, 2018 24

በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን፣ መከባበርንና የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እውነትንና አብሮ መኖርን መሠረት ያደረጉ የምክክርና የውይይት መድረኮች መተኪያ የሌለው ሚና እንዳላቸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የመንበረ ፓትርያርክ የጥናትና ምርምር ኃላፊ መምህር ዳንኤል ሰይፈሚካኤል ገለጹ።

ኃላፊው በሀገራዊ አብሮነት፣ በሃይማኖታዊ እሴቶችና በምክክር አስፈላጊነት ላይ በሰጡት ማብራሪያ፤ ውይይት በማንኛውም የሰው ልጅ ማኅበራዊ ሕይወት ውስጥ መሠረታዊና ወሳኝ መሣሪያ መሆኑን ገልጸው፣ መመካከርና መወያየት በማንኛውም ጊዜና ሁኔታ ውስጥ ቀዳሚ ቦታ ሊሰጠው የሚገባ ተግባር መሆኑን አብራርተዋል።

መምህር ዳንኤል አያይዘውም "ከሁለት ሰዎች ተስማምቶ ከመኖር ጀምሮ በሀገር ደረጃ እንኳን ሳይቀር፣ እውነትንና አብሮ መኖርን መሠረት አድርገው የሚደረጉ ውይይቶችና መመካከሮች ዓለም አቀፍ እሴት አላቸው" ብለዋል።

በብዙ ሀገራት ታሪክ ውስጥ መልካም ለውጦች፣ ዘላቂ ስምምነቶች፣ መተማመንና መከባበር የተገነቡት እንዲሁም የጋራ ሀብቶችን በፍትሐዊነት ማስተዳደር የተቻለው በውይይት በተገኙ መፍትሔዎች መሆኑንም አውስተዋል።

በኢትዮጵያም ቢሆን የሁሉንም ዜጎች ተሳትፎ ያረጋገጠ የውይይት ባህልን ማሳደግ ትልቅ ሀገራዊ ተስፋ እንደሚሰጥ የጠቆሙት መምህር ዳንኤል፤ ለአንዲት ሀገር የሚደረግ የጋራ ጥረትና የወል ተጠቃሚነትን ያስቀደመ መመካከር ሀገራዊ አንድነትን ይበልጥ እንደሚያጠናክር አስረድተዋል።

ሀገራዊ ችግሮችንና ልዩነቶችን በበሰለ ውይይት ለመፍታት የሚደረጉ ጥረቶች ውጤታማ ሊሆኑ የሚችሉት የሁሉም ወገን ቅን ፍላጎትና እውነተኛ ተሳትፎ ሲታከልበት መሆኑንም አጽንኦት ሰጥተውበታል።

በመሆኑም ከጠመንጃና ከግጭት አማራጮች ይልቅ በጠረጴዛ ዙሪያ የመቀመጥ ባህል ሲዳብር፣ የጋራ ሀብቶችን በፍትሐዊነት የመጠቀምና የነገዋን ኢትዮጵያ በተስፋ የመገንባት ዕድል በእጅጉ እንደሚሰፋ አስገንዝበዋል።

በሃይማኖት ከበደ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: