የቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ለ120 ሺህ ዜጎች ነፃ ሕክምና እና ልዩ ልዩ ድጋፎች የሚሰጥበትን የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መርሐ ግብር በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ በይፋ አስጀምሯል።
የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር መቅደስ ዳባ በማስጀመሪያው መርሐ ግብር ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር፣ በርካታ ዜጎች የዕድሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ሚኒስቴሩ ከሆስፒታሉ ጋር በቅንጅት እየሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ዜጎችም በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ በንቃት እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።
የቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር አብርሃም እሸቱ በበኩላቸው፤ አገልግሎቱ በርካታ አጋር አካላት የተሳተፉበት መሆኑን ጠቁመው፣ በመርሐ ግብሩ 120 ሺህ ዜጎች የነፃ ሕክምና አገልግሎት ያገኛሉ ብለዋል።
ከሕክምና አገልግሎቱ በተጨማሪ የአቅመ ደካሞችን ቤት ማደስ፣ የችግኝ ተከላ እና ሌሎች ማኅበራዊ በጎ ተግባራት መካተታቸውንም ተናግረዋል።
በዛሬው ዕለት በተጀመረው መርሐ ግብር ላይ ከተለያዩ የጤና ተቋማት የተወጣጡ የሕክምና ባለሙያዎች በቅዱስ ጴጥሮስ ሆስፒታል ተገኝተው ለኅብረተሰቡ ነፃ የሕክምና አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል።
የጤና ሚኒስቴር ባለፈው ሳምንት የበጀት ዓመቱን የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በሸገር ከተማ አስተዳደር በሚገኘው የዳለቲ ማረሚያ ቤት በይፋ ማስጀመሩ ይታወሳል።
በመሃሪ ዓለሙ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: