Search

ሩሲያ በ7.2 ሚሊዮን ዶላር ለአሜሪካ የሸጠቻት አላስካ

Aug 17, 2025

የአሜሪካ እና ሩሲያ መሪዎች ሰሞኑን ለውይይት የመረጧት አላስካ ግዛትን ሩሲያ በሔክታር ከአምስት ሳንቲም ባነሰ ዋጋ ለአሜሪካ የሸጠቻት መሆኑን ያውቃሉ? 

እ.አ.አ ከ1853-1856 ሩሲያ ከክሪሚያ ጋር አድርጋው በነበረው ጦርነት መሸነፏን ተከትሎ አጋጥሟት በነበረው የኢኮኖሚ አለመረጋጋት እና ብሪታኒያ አላስካን ለመንጠቅ ጦርነት ልትከፍትብኝ ትችላለች በሚል ስጋት ግዛቷ የነበረችውን አላስካን ለአሜሪካ ለመሸጥ ወሰነች። 

እናም ፈረንጆቹ አቆጣጠር በ1867 አላስካ አንዱን ሔክታር ከአምስት ሳንቲም በታች በሆነ ዋጋ በአጠቃላይ በ7.2 ሚሊዮን ዶላር ለአሜሪካ ተሸጠች። 

የአሜሪካ መንግሥት ይህንን ግዥ መፈፀሙን ተከትሎ በወቅቱ ከሀገር ውስጥ ተቃውሞ ገጥሞት ነበር። 

“አንዳች ፋይዳ የሌለው፤ በበረዶ የተሸፈነ መሬት ላይ ይህን ያህል ገንዘብ ማባከን አግባብ አይደለም” ሲሉ ብዙዎች ተቃወሙት።

የሕዝቡ ቅሬታ የተቀየረው የአሜሪካ መንግሥት አላስካን ከገዛ ከ23 ዓመታት በኋላ (ማለትም እ.አ.አ በ1890) በግዛቲቱ ከርሰ-ምድር የወርቅ ማዕድኖች ካገኘ በኋላ ነበር።

ከዓመታት በኋላም አላስካ ነዳጅ፣ ዘይት እና ውድ የሆነ የዓሣ ክምችት ያለባት መሆኗ ታወቀ። ይህን ተከትሎም ብዛት ያላቸው አሜሪካውያን ወደ አላስካ መጉረፍ ጀመሩ። 

እ.አ.አ ጃንዋሪ 3/1959 ላይም አላስካ 49ኛ የአሜሪካን ግዛት ሆና በይፋ እውቅና አገኘች።

አሁን ላይ በውስጧ በያዘችው እምቅ ማዕድናት እና በወታደራዊ ጠቀሜታዋ ትልቅ ቦታ ያላት አላስካ አሜሪካ ካሏት ግዛቶች በሙሉ በስፋቷ ተወዳዳሪ የሌላት ሲሆን በቆዳ ስፋቷ ቴክሳስ እና ካሊፎርኒያ ግዛቶች እንኳን ቢደመሩ አይደርሱባትም። 

እንደውም አላስካ ሀገር ብትሆን በዓለም ላይ በያዙት የቆዳ ስፋት የሚበልጧት 18 ሀገራት ብቻ ናቸው። በአህጉራችን አፍሪካ የአላስካን ስፋት ያህል የቆዳ ስፋት ያላት ሊቢያ ብቻ ናት። 

በአንድ ወቅት “በሔክታር ከአምስት ሳንቲም ባነሰ ዋጋ” የተሸጠችው አላስካ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ግዙፍ እና ትናንሽ የውኃ አካላት በውስጧ የያዘች ናት። 

ከነዚህ የውኃ ሀብቶችም በዓለም ላይ እጅግ ውድ የሆነው የሳልመን እና ክራብ የዓሣ ዝርያዎችን ጨምሮ በዓመት 2 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ዓሣ ታመርታለች። 

ስድሳ በመቶ የሚሆነው ለአሜሪካ የሚያስፈልጋት የዓሣ ፍጆታም የሚገኘው ከዚሁ ከአላስካ ነው። 

በአንድ ወቅት ጥቂት ሰዎች ብቻ ይኖሩባት የነበረችው አላስካ አሁን ላይ 741 ሺህ በላይ ሕዝብ የሚኖሩባት ግዛት ሆናለች። 

በዋሲሁን ተስፋዬ 

#EBC #ebcdotstream #usa #alaska