Search

አርቲስት ደበበ እሸቱ ከዚህ ዓለም ድካም አረፉ

እሑድ ነሐሴ 11, 2017 154

በኪነ-ጥበቡ ዓለም ታላቅ ዐሻራቸውን ያሳረፉት ክቡር ዶክተር አርቲስት ደበበ እሸቱ ማረፋቸውን ከቤተሰባቸው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ክቡር ዶክተር አርቲስት ደበበ እሸቱ ለሀገራቸው ያላቸውን የማይናወጥ ፍቅር እስከ እስትንፋሳቸው መጨረሻ ያሳዩ ፅኑ ሀገር ወዳድ ነበሩ።
የታሪክ ድርሳናቸው እንደሚያስረዳው አርቲስት ደበበ እሸቱ በ1934 ዓ.ም ነው የተወለዱት። የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አዲስ አበባ በሚገኘው ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ተከታትለዋል።
በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ተማሪ እያሉ ቲያትር የመስራት ዕድሉ ገጥሟቸው ነበር።
ከዛ በመቀጠል የአብራሪነት ስልጠና ለመውሰድ እጩ መኮንን ሆነው የኢትዮጲያ አየር ሀይልን ተቀላቀሉ። በአየር ኃይል የመዝናኛ ክፍሉ ላይ በመሳተፍ ቲያትር ሰርተዋል።
አርቲስት ደበበ እሸቱ፤ በሀገር ፍቅርና በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ (የአሁኑ ብሔራዊ ቴአትር) መድረክ ላይ ለረዥም ዓመታት በተዋናይነትና በአዘጋጅነት አገልግለዋል።
በተለያዩ ፊልሞች ላይ በመሪ ተዋናይነትም ተሳትፈዋል። በሆሊውድ በተሠራው 'ሻፍት ኢን አፍሪካ' በተሰኘው ፊልም ላይ በመሳተፍም ስማቸውን በደማቁ ፅፈዋል።
በእንግሊዘኛ ከሠሩባቸው ፊልሞች መካከል 'ዘ ሴይለር ፍሮም ጂብራልታር'፣ 'ጉማ'፣ 'ዘ አፍሪካን ስፓይ'፣ 'ዜልዳ'፣ 'ዘ ግሬቭ ዲገር' እና 'ዘ ግሬት ሪቤሊየን ' ይጠቀሳሉ።
'ዘ ጌም ኦፍ ቼዝ' ላይ በትወና ፣ 'ኦቴሎ' ላይ በመተወን እና በማዘጋጀትም የጥበብ አሻራቸውን አኑረዋል።
ደበበ እሸቱ ከአርቲስቱ በተጨማሪ በራድዮና በቴሌቪዥን ሥራዎችም ላይ ተሳትፈዋል። 'ያላቻ ጋብቻ'፣ 'ሮሚዎና ዡልየት' እና 'ዳንዴው ጨቡዴ' ከተወኑባቸው ሥራዎች ጥቂቶቹ ናቸው።
አርቲስት ደበበ እሸቱ እ.አ.አ. በ1985 ዚምባቡዌ በተካሄደው ቴአትር ለልማትና ዕድገት ወርክሾፕ ላይ በብቃት በመሳተፍ የአፍሪካ የመድረክ ባለሙያዎች ማሕበርን አስተባብረው በማቋቋም የማሕበሩም መስራች ፕሬዚዳንት ሆነው ለ12 ዓመታት አገልግለዋል፡፡
ለአፍሪካ ቲያትር ባደረጉት አስተዋጽኦ የዚምባብዌን ማላካይት አዋርድ ወስደዋል። ጣይቱ ኢንተርቴንመንት በዋሽንግተን ዲሲ በቲያትር ዘርፍ የሕይወት ዘመን ተሸላሚ አድርጓቸዋል፡፡
በአትላንታ ጂኦርጂያ የከተማው ምክር ቤት ለዓለም ቲያትር ባደረጉት አስተዋጽኦ ኖቬምበር 24ን የደበበ እሸቱ ቀን በሚል ሰይሞላቸዋል፡፡
የኢትዮጲያ ባህል ሚኒስትርም ለኢትዮጲያ ፊልም እድገት ላበረከቱት አስተዋጽኦ ሸልሟቸዋል፡፡
በጉማ አዋርድም የሕይወት ዘመን ተሸላሚ ሆነዋል፡፡
እ.አ.አ በ2015 በቫንኮቨር ዓለማቀፍ ፊልም ፌስቲቫልም በምርጥ መሪ ተዋናይ ዘርፍ ተሸላሚ ሆነዋል፡፡ በ2015 ዓ.ም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለሃገራቸው ባበረከቱት አስተዋጽኦ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ሸልሟቸዋል።
አርቲስት ደበበ እሸቱ በ1995 ዓ.ም በሃገራዊ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ውስጥ በመሳተፍ የምክር ቤት አባል እና የፓርቲያቸው የሕዝብ ግንኙነት በመሆን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረጉ ሰው ናቸው። በዚህም ከሌሎች አመራሮች ጋር በተለያዩ ጊዜያት ለእስር ተዳርገው ነበር።
ኢቢሲ ለቤተሰባቸው፣ ለወዳጅ ዘመድ እና ለመላው አድናቂዎቻቸው መጽናናትን ይመኛል።
የኢፌዲሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር በኢትዮጵያ የኪነ ጥበብ ታሪክ ውስጥ ጉልህ ሚና ከተጫወቱ አንዱና ግንባር ቀደሙ አንጋፋው የመድረክ ፈርጥ፣ ደራሲ፣ ተርጓሚ፣ ተዋናይ፣ ከያኒ፣ ጋዜጠኛ፣ የመብት ተሟጋች እና ሀገር ወዳዱ የክብር ዶክተር አርቲስት ደበበ ህልፈተ ሕይወት የተሰማውን ሐዘን ገልጿል።
በ83 ዓመታቸው ባደረባቸው ህመም ምክንያት በህክምና ሲረዱ ቆይተው ከዚህ ዓለም ድካም ማረፋቸውን በመስማታችን ታላቅ ሀዘን ተሰምቶናል ሲልም ሚኒስቴሩ መግለጫ አውጥቷል።