ዘመናት ተሻግረው በደም እና በአጥንት የቆሙ ሀገራት የሚፈተኑት በውጭ ጠላቶቻቸው ወረራ ብቻ አይደለም። ትልቁና አደገኛው ፈተና ከውስጥ የሚበቅለው የጥላቻ አረም፣ የፖለቲካ መሰረት መሸርሸር እና የሕዝብ እምነት መላላት ነው። ኢትዮጵያም በዚህ መንገድ ተፈትና አልፋ ታውቃላች፡፡
የሀገር ትልቁ የደኅንነት ስጋት የዉጭ ወታደራዊ ወረራ ብቻ አይደለም። ትልቁ ጠላት በሕጋዊ ሉዓላዊነት እና በሕዝባዊ ባለቤትነት መካከል ያለው ገደል ነው። ይህ ገደል በሰፋ ቁጥር የውጭ ኃይሎች፣ የታሪክ አጋጣሚን የሚጠብቁ ቀጠናዊ ተፎካካሪዎች እና የውክልና ጦር አዝማቾች በቤታችን ጣሪያ ላይ ቀዳዳ ያገኛሉ። የውስጥ አለመግባባታችንን የዓለም አቀፍ ድራማ፣ የእርስ በእርስ ግጭታችንን ደግሞ የራሳቸው የፖለቲካ መደራደሪያ ያደርጉታል፡፡
ኢትዮጵያ ታላቅ ሕዝብ፣ ሰፊ የቆዳ ስፋት፣ ቁልፍ ጂኦ-ፖለቲካዊ ቦታ እና የተከበረ ወታደራዊ ታሪክ አላት። ከዚህ መልካም ታሪክ በተቃራኒው ደግሞ በርካታ ያቆሰሏትን ወጀቦችና ፈተናዎችን አልፋለች፡፡ አሁንም ኢትዮጵያ የውስጥ ቁስሏን በገዛ እጇ ካልጠገነች፣ "የውጭ ሀኪም ነን" ባዮች መርዛቸውን ይዘው መምጣታቸው አይቀሬ ነው፡፡
"የውስጥ ስምምነት እንደ ስትራቴጂካዊ መከላከያ" የሚለው ጽንሰ ሐሳብ የሚመጣውም እዚህ ጋር ነው። ይህ መከላከያ ታንክና ሚሳኤል አይደለም፤ ይልቁንም የውጭ ኃይሎች አጀንዳቸውን በሀገራችን ላይ የማስቀመጥ አቅማቸውን መስበር ነው፡፡
በአዲስ አበባ የተጀመረው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤም፣ ይህ የውጭ ኃይሎች አጀንዳ የማስቀመጥ አቅም የሚሰበርበት ወርቃማ ዕድል ነው፡፡ ይህ መድረክ ኢትዮጵያ በውጥረትና አለመረጋጋት በሚታመሰው የቀይ ባሕር ቀጠና እና በታላቁ የአፍሪካ ቀንድ የምታሳየውን ቀጣናዊ ሚና የበለጠ የሚታጠናክርበት የሉዓላዊነት ጋሻ ነው፡፡
አካታች የሆነ የፖለቲካ ውይይት ሕዝባዊ ቅቡልነትን ይፈጥራል፤ ሕዝባዊ ቅቡልነት ደግሞ የተቋማትን ፅናት ያጠናክራል፤ የተቋማት ፅናትም የውጭ ተፅዕኖንና ጫናን ይቀንሳል። የቀነሰ የውጭ ጫና ደግሞ ሙሉ ስትራቴጂካዊ ነፃነትን ያጎናፅፋል፡፡
ኢትዮጵያ በውስጧ የጠነከረ ብሔራዊ መግባባት ካላት ስለ ባሕር በር ስትደራደር አቅሟ ሙሉ ይሆናል፡፡ በዓለም አቀፍ መድረኮች ስትናገር ድምጿ ይጎላል፡፡ ተገዳዳሪ የደኅንነት አደጋ ሲገጥማትም አሸናፊ ትሆናለች፡፡ በታላቁ የቀይ ባሕር ደህንነት ጉዳይ ላይ ከዓለም አቀፍ ኃይሎች ጋር እኩል፣ በራስ መተማመን ትቀመጣለች፡፡
ሀገር ማለት ሕዝብ የተስማማበት ህያው አካል ነው፡፡ የሀገራዊ የምክክር መድረኩ ዋና እሴት ቁስሎችን ሽሮ በጋራ ሀገር መገንባት እንጂ በግዳጅ የተሰራ አንድነት መፍጠር አይደለም። ይልቁንም፣ ልዩነቶችን በሰለጠነ መንገድ በጠረጴዛ ዙሪያ አምጥቶ በመወያየት የሀገርን መዋቅር ማደስ ነው፡፡
ስለዚህም የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር መድረክ የተለመደው የሕዝብ ግንኙነት ስራ አይደለም፤ ይህ መድረክ እውነተኛ የሀገራዊ ደኅንነታችን የጀርባ አጥንት ነው፡፡
የኢትዮጵያ ስትራቴጂካዊ ነፃነትና ታላቅነት በወደቦች፣ በድንበሮች ወይም በወታደራዊ ሰፈሮች ብዛት ብቻ አይወሰንም። እውነተኛው ነፃነት የሚረጋገጠው ኢትዮጵያውያን ልዩነቶቻቸውን በጦርነት ሳይሆን በሰለጠነ ተቋማዊ መንገድ መፍታት የሚችሉ መሆናቸውን ለዓለም ሲያሳዩ ነው፡፡
በመሆኑም ኢትዮጵያውያን ይህንን ወርቃማ ዕድል ለሀገር ህልውና መረጋገጥ ሊጠቀሙበት ይገባል፡፡ ልዩነት ተፈጥሯዊ ነው፤ የምክክሩ የመጨረሻ ውጤት የሚለካውም "ልዩነትን አጠፋ ወይ?" በሚለው ሳይሆን "ምክክሩ እዉነተኛ ሀገራዊ አንድነትና ደኅንነትን መገንባት ቻለ ወይ?" በሚለው ነው።
በንብርቴ ተሆነ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: