በ21ኛው ክፍለ ዘመን የአንድን ሀገር የመደራደር አቅም የሚበይነው በከርሰ-ምድሯ ውስጥ ያለው የማዕድን ሀብት አልያም ነዳጅ ብቻ ሳይሆን፣ በሰርቨሮቿ ውስጥ የሚዘዋወረው የዳታ (መረጃ) ክምችት ነው ብባሉ ሊያምኑ ይችላሉ ?
በእርግጥም ዳታ የዘመናችን እጅግ ውድ ሀብት እና የነገውን ዓለም የጂኦ-ፖለቲካዊና የኢኮኖሚ አቅጣጫ የሚወስን የቀጣዩ ዘመን መሳሪያ ሆኗል። ይህ የዘመናችን ሃቅ የኢትዮጵያ መንግሥት በአሁኑ ወቅት የጀመረውን ታሪካዊ ሽግግር ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ሲሆን፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንዳስረዱት፣ ኢትዮጵያ ከባህላዊ እና ግምታዊ የአስተዳደር ሥርዓት ወደ ትክክለኛ እና መረጃ-መር አስተዳደር በመሸጋገር ላይ ትገኛለች።
በርካታ አዳጊ ሀገራት የፖሊሲ ውሳኔዎቻቸውን የሚያሳልፉት በዓለም አቀፍ ተቋማት በሚሰጧቸው የተገመቱ ዳታዎች ላይ ተመስርተው መሆኑ ከፍተኛ የፖሊሲ ጥገኝነትን አስከትሏል።
ይህን ታሪካዊ ስህተት ለማረም፣ ዳታ የሀገር ሉዓላዊነት ማስጠበቂያ እና የፖሊሲ ነፃነት ማረጋገጫ የጀርባ አጥንት መሆኑን መገንዘብ ግድ ይላል። "ዳታ የአዲሱ ዘመን ነዳጅ ነው" የሚለው ዓለም አቀፋዊ ፅንሰ-ሐሳብ ወደ "ዳታ የአዲሱ ዘመን ሉዓላዊነት ነው" ወደሚል ሀገራዊ እሳቤ ያደገውም ለዚሁ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ "ዳታ ተውሶ የፖሊሲ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ አይቻልም" በማለት የገለጹትም፣ ሉዓላዊነት የሀገር ድንበርን ከመጠበቅ ባለፈ የራስን ብሔራዊ መረጃ በራስ አቅም ማሰባሰብ እና ደኅንነቱን ጠብቆ ማስተዳደርን የሚጠይቅ የዲጂታሉ ዘመን የኅልውና ጉዳይ በመሆኑ ነው።
ይህን የዲጂታል ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ ኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ትልልቅ ስትራቴጂያዊ እርምጃዎችን ስትወስድ ቆይታለች። የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩትን በመገንባት የተጀመረው ጉዞ የብሔራዊ መታወቂያ (ፋይዳ) ሥርዓት ትግበራን በማፋጠን፣ በኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት (INSA) በኩል የሳይበር አቅምን በማጎልበት፣ ግዙፍ ብሔራዊ የዳታ ማዕከላትን (National Data Centers) በመገንባት እንዲሁም የቴሌኮም ዘርፉን በማስፋፋት ለዲጂታል ኢኮኖሚው ጠንካራ መሠረት ጥሏል።
የዚህ ጥረት ቀጣይ ምዕራፍ የሆነው የስታትስቲክስ አገልግሎት የሀገራችን መረጃዎች በድሮን፣ በሳተላይት፣ በጂኦ-ስፓሻል (GIS) እና በአካል በመገኘት ማሰባሰቡ እንዲሁም ከተለያዩ ምንጮች ማመሳከሩ በዳታ ሳይንስ ውስጥ የተሳሳተ መረጃን አደጋ ለማስቀረት ወሳኝ እመርታ ነው።
መረጃ ሰብሳቢዎችን በቴክኖሎጂ ታግዞ መከታተሉ ደግሞ የዳታውን ጥራት ከፍ ከማድረጉም ባሻገር፣ የሀገራችንን ትክክለኛ የኢኮኖሚ አቅምና አጠቃላይ ሁኔታ ለዓለም አቀፍ ገበያ በማቅረብ ጠንካራ የኢንቨስትመንት መደራደሪያ አቅም ይፈጥራል።
የዳታ ሳይንስ ትልቁ ግብም ቁጥሮችን መደርደር ብቻ ሳይሆን፣ በቁጥሮቹ ጀርባ ያለውን የሰው ልጅ የኑሮ ዘይቤ ተረድቶ ትክክለኛ ፖሊሲ መንደፍ ነው።
መረጃ እጅግ ውድ እና የቀጣዩ ዘመን ዋና መሳሪያ የሚሆነውም ከዚህ አቅሙ የተነሳ ነው። ይህን ውድ ሀብት ወደ ተጨባጭ የህይወት ለውጥ ለመቀየር ደግሞ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) እና የማሽን መማሪያ ቴክኖሎጂዎች ግብርናን፣ ጤናን እና ኢኮኖሚን በማስተሳሰር ረገድ ያላቸው ሚና የማይተካ ነው።
ይህ ሀገራዊ ራዕይ የተሟላ ስኬት እንዲያመጣ እና ዳታ በእርግጥም የሀገርን ብልፅግና የሚያረጋግጥ የአዲሱ ዘመን 'ወርቅ' እንዲሆን፣ ከመረጃ ክፍትነት እና ደኅንነት ጋር የተያያዙ ሥራዎች ይበልጥ በትኩረት ሊሠሩ ይገባል።
ይህን የተሰበሰበ ግዙፍ መረጃ (Big Data) ከሳይበር ጥቃት የሚጠብቅ እና በሥነ-ምግባር የሚመራ የህግ ማዕቀፍ በጥብቅ ተግባራዊ መደረግ አለበት።
ከዚህ ጎን ለጎንም መረጃውን ተጠቅመው ትንበያዎችን መሥራት የሚችሉ ከፍተኛ የዳታ ሳይንቲስቶችን ለማፍራት እና የክላውድ ኮምፒውቲንግ መሠረተ ልማቶችን ለማስፋፋት የተጀመሩ ጥረቶችን አጠናክሮ መቀጠል የግድ ይላል።
በዚህም ዳታን መሰብሰብ ብቻ ሳይሆን፣ በዘመናዊ ዳሽቦርድ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ማቅረብ መቻሉ፣ አመራሩ ፈጣን እና መረጃ ላይ የተመሰረተ ውሳኔ እንዲሰጥ በማስቻል ኢትዮጵያን በቴክኖሎጂ ወደተደገፈ ዘመናዊ፣ ሉዓላዊ እና ትክክለኛ አስተዳደር በፍጥነት ያሸጋግራታል።
በበረከት ሽመልስ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: