Search

ከኃይል ስሌት ወደ ሰለጠነ ውይይት፤ የመተማመንና የጋራ ዕድገት መንገድ

እሑድ ሐምሌ 19, 2018 51

የኢትዮጵያን ዘመናት የተሻገሩ ቁርሾዎች፣ የፖለቲካ ልዩነቶችና የማንነት ጥያቄዎች በዘላቂነት ለመፍታት የተቋቋመው የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን፤ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሥራውን አጠናቆ በአሁኑ ወቅት ወደ እጅግ ወሳኝ የውይይት ምዕራፍ ተሸጋግሯል።

ዛሬ ላይ ኢትዮጵያዊ በዓለም ሕዝብ ፊት በማንነቱ የሚኮራው ቀደምት አባቶች ባስቀመጡለት በጎ ዐሻራ ቢሆንም ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብርን የሚያበላሹ የተሳሳቱ ትርክቶች የሀገራችንን ገጽታ ለማጠልሸት መንስኤ እየሆኑ መምጣታቸው ይስተዋላል።

ኢትዮጵያ የተለያዩ ማንነቶች ላቸው ሕዝብ ሀገር መሆኗን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ሕብረተሰቡን እርስ በርስ እንዲጠራጠርና ልዩነቶችን እንደ ስጋት ምንጭ እንዲያይ ከውጭና ከውስጥ የሚሰነዘሩ የተዛቡ ትርክቶችንና የጽንፈኝነት ዕይታዎችን ለመቀልበስ የሥልጣኔ መገለጫ የሆነው የጠረጴዛ ዙሪያ ውይይት ብቸኛው አማራጭ ነው።

ሀገራዊ ምክክሩ የሀሳብ ልዩነቶችን በአሸናፊ ተሸናፊ ስሌት እና በኃይል ለመፍታት ከመሞከር በመውጣት ከመጠፋፋት ወደ ሰለጠነ ሰላማዊ እና አካታች ሀገራዊ አውድ ለመሸጋገር የተገኘ ታሪካዊ እድል ነው።

ይህ መድረክ ዜጎች በሀሳባቸው ለውጥ ማምጣት እንደሚችሉ እንዲያምኑ ከማድረጉም በላይ በመንግሥት እና በሕዝብ መካከል ያለውን መተማመን ያጠናክራል።

በአካታች ባህሪውም የፖለቲካ ፓርቲዎች የሲቪክ ማህበራት የሃይማኖት አባቶች ሴቶችና ወጣቶች እኩል ድምፃቸው የሚሰማበትና በዐበይት ሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ የጋራ መቋጫ የሚፈለግበት መንገድም ጭምር ነው።

በውይይትና በምክክር ችግሮቹን መፍታት የቻለ ሕብረተሰብ ለሰላም ዘብ በመሆን ሀገርን ከመታደጉም ባሻገር ለዲፕሎማሲ ከፍታ የሚተጋና የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ለማሳደግ በጋራ የሚቆም በመሆኑ በአሁኑ ወቅት እየተካሄደ ያለው ጉባኤ ለቀጣዩ ትውልድ የተሻለችና የበለፀገች ሀገርን ለማስረከብ ትልቅ መሠረት እንደሚጥል ይታመናል።

በብሌን ደምበሎ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: