Search

የሕገ ወጡ ህወሓት የሥልጣን ጥማት እና የትግራይ ሕዝብ እውነት

እሑድ ሐምሌ 19, 2018 42

አንድን ሀገር፣ ሀገር የሚያሰኘው የድንበር መስመር ወይም የመሬት ስፋት ብቻ ሳይሆን፣ በውስጧ የሚኖሩ ሕዝቦች በጋራ የገነቡት ታሪክ፣ የተጋሩት ዕጣ ፈንታ፣ የደሙለት ሰንደቅ ዓላማ እና በክፉም በደጉም አብረው የቆሙበት የኅልውና ትስስር ነው።

ሆኖም ባለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ምህዳር ውስጥ ይህንን ታሪካዊ እውነት ያጠለሹ፣ ሀገር የሚያፈርሱ እና ሕዝብን እርስ በእርስ የሚያናቁሩ አጀንዳዎች ሲስተናገዱ ቆይተዋል።

ለዚህ አፍራሽ ሚና ደግሞ በዋና ተዋናይነት የሚጠቀሰው ሕገ ወጡ የህወሓት ቡድን ሲሆን፣ ቡድኑ በ2013 ዓ.ም በከፈተው ጦርነት በኢትዮጵያ ላይ ከፍተኛ በደል ፈጽሟል።

በዚህም የበርካቶች ሕይወት አልፏል። የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሀብትና መሠረተ ልማት ወድሟል። ቡድኑ ሥልጣን ላይ ከነበረበት ጊዜ ጀምሮ ሀገርን በመመዝበር የኢኮኖሚ አውታሮች የውጭ ብድርና እርዳታዎችን በጥቂት አባላቱ እና ተቋማት ሥር ሲያከማች ቆይቷል።

ከሥልጣን ሲወገድም፣ ሀብት በማሸሽ እና በማውደም ኢትዮጵያን በኢኮኖሚ በመበዝበዝ በተለያዩ ጊዜያት ያደረሰው የመሠረተ ልማት ውድመት የዚሁ ጥፋት ማሳያዎች ናቸው።

ከዚህም ባለፈ፣ ሀገር ለማፍረስ የራስን ታጣቂ ኃይል መገንባት እና የራስን ብቸኛ ነጻነት ለማወጅ ቅድመ ዝግጅት ሲያደርግ ቆይቷል።

በተለይም ቡድኑ የትግራይን ወጣቶች በሐሰት ፕሮፖጋንዳ በማነሳሳት ለጦርነትና ለሞት የዳረገ ሲሆን፣ አሁንም ቢሆን የፈረመውን የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ጊዜ በመግዛትና ስምምነቱን በመጣስ ለሌላ ዙር ጦርነት ሰፊ ዝግጅት እያደረገ ይገኛል።

የቀሩትን ወጣቶች ለጦርነት ማገዶ ለማድረግ አስገድዶ ወደ ጦር ማሠልጠኛ ማዕከላት አፈሳ እያደረገሲሆን፣ የቡድኑን ሴራ እና አፍራሽ ዓላማ የተገነዘበው የትግራይ ክልል ሕዝብም ከሕጻን እስከ አዋቂ ቡድኑን በጽኑ እየተቃወመ ይገኛል።

ወጣቶች ከአስገዳጅ አፈሳው ለማምለጥ የራሳቸውን ስልት ቀይሰው በሕብረት ራሳቸውን እያቀቡና እየተከላከሉ ሲሆን፣ እናቶችም "ልጆቻችንን ለጦርነት አንሰጥም" በማለት ፊት ለፊት ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።

በተጨማሪ ከክልሉ ውጭ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች፣ የማኅበራዊ ሚዲያ ጸሐፊዎች፣ ዲያስፖራዎችና አርቲስቶች "የትግራይ ሕዝብ ሰላም ይፈልጋል፤ ጦርነት ይብቃ" በማለት የቡድኑን የጦርነት ዝግጅት አውግዘዋል።

በመሆኑም ትልቁ እና ወሳኙ ነጥብ የአንድ ቡድን የሥልጣን ጥማት መላውን የትግራይ ሕዝብ ሊወክል አይችልም። የትግራይ ሕዝብ ከመላው የኢትዮጵያ ወንድምና እህቱ ጋር በጋብቻ፣ በሃይማኖት፣ በባሕል እና በታሪክ የተሳሰረ ነው።

አሁን ያለንበት ወቅት እውነትን ከሐሰት ለይተን የምንቆምበት እና ትግሉ ከሕዝብ ጋር ሳይሆን፣ ከአፍራሽ ሐሳቦች ጋር ነው።

ኢትዮጵያ ለሁሉም ልጆቿ የምትበቃ፣ በፍቅር እና በፍትሕ የምትመራ ሀገር ልትሆን የምትችለው እንዲህ ያሉትን ከፋፋይ ኃይሎች በጋራ መታገል ሲቻል ነው። ይህን አካል ቆርጦ ለመጣል የሚሞክረውን የጥፋት መንገድ በጋራ ማረም የመላው ኢትዮጵያውያን ታሪካዊ ኃላፊነት ነው።

በብሌን ደምበሎ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: