Search

ከአቋማቸው ዝንፍ የማይሉት የጥበብ ሰው አርቲስት ደበበ እሸቱ ሲታወሱ?

እሑድ ነሐሴ 11, 2017 2295

በኢትዮጵያ የቴአትር እና የፊልም ታሪክ ትልቅ ዐሻራን ያሳረፉት፤ ሀገራቸውን በሙሉ ልባቸው የሚወዱት እና ያገለገሉት ብሎም በነፈሰው ሳይነፍሱ ከሀገራቸው ጎን የቆሙት አርቲስት ደበበ እሸቱ ከዚህ ዓለም በሞት  ተለይተዋል።

የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴዔታ ነብዩ ባዬ ሀዘናቸውን በገለጹበት ወቅት "አርቲስት ደበበ የሀገር ወዳድነት ማሳያ ብቻ ሳይሆን፤ ያለውን ልምድና ዕውቀት ያለስስት ለወጣቶች ያጋራ ነው። ሲሉ ተናግረዋል።

በዓለምአቀፍ ፊልሞች ላይ የተሳተፉት ኢትዮጵያን እና አፍሪካን በጥበቡ ዓለም ተቋማት የወከሉት የበጎ ሥራ አምባሳደሩ፤ ሕዝብ ነጻ ለማውጣት ወደ ፖለቲካም የገቡት አርቲስት ደበበ እሸቱ እንዲህ ይታወሳሉ፦

በ1934 ዓ.ም የተወለዱት አርቲስት ደበበ እሸቱ፤ የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ተከታትለዋል። አርቲስት ደበበ የቴአትር ጥበብ ጅማሮአቸውም በዚሁ በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት እንደሆነ ይነሳል።

አርቲስት ደበበ እሸቱ ቴአትር የሕይወት ዘመናቸው ጥሪ መሆኑን በጊዜው እንዳላስተዋሉም በቃለ መጠይቆች ላይ ተናግረዋል። ከዛ በመቀጠል የአብራሪነት ስልጠና ለመውሰድ እጩ መኮንን ሆነው የኢትዮጲያ አየር ኃይልን ቢቀላቀሉም፤ በአየር ኃይል የመዝናኛ ክፍል አባል በመሆን ከቴአትር ጋር ያላቸውን ቁርኝት አስቀጥለዋል።

አርቲስት ደበበ የአየር ኃይል ትምህርታቸውን አቋርጠው በፖስታ ቤት ሥራ ተቀጥረውም ሰርተዋል። በአየር ኃይል ያቁረጡት ትምሕርት ሊያሳሥራቸው ስለሚችልም ወደ ደብረብርሃን አቅንተው የመምህርነት ስልጠና መከታተል ጀመሩ።

በወቅቱ የማስልጠኛው ተማሪዎቹ ተቃውሞ በማስነሳታቸው አርቲስት ደበበም የዚሁ ተቃውሞ አባል ስለነበሩ፤ ለቅጣት ተዳርገው የፖለቲካ እስረኛ ሆነው ጎሬ ተላኩ።

እስር የአርቲስቱን ሕልም አሁንም አልጋረደውም፤ ከእስር እንደተፈቱ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፐርፎርሚንግ አርትስ መማር ጀመሩ። የሀገር ውስጡን ትምህርታቸውንም አጠናቀው እ.አ.አ በ1965 ደግሞ ወደ ሃንጋሪ በማቅናት የቴአትር ጥበብን ከውጭ ሀገርም ቀነሱ። 

በሃንጋሪ ቆይታቸው ካገኙት ትምህርት በላይ የሃገራቸውን ልጆች እነ ተስፋዬ አውላቸው፣ ጌታቸው ደባልቄ፣ አስካለ አመነሸዋ እና ሌሎች ቀደምት ሙያተኞችን በማግኘታቸው ብዙ እውቀት መቅሰማቸውን ይናገራሉ። 

ደራሲ፤ ተርጓሚ፤ አዘጋጅ፤ ተዋናይ፤ መድረክ መሪና ሁለገብ አርቲስት ደበበ እሸቱ የቴአትርን ሥራ በቀድሞው ክሬቲቭ አርት ሴንተር ባሁኑ ባህል ማዕከል በይፋ ከጀመሩ ወዲህ ለኢትዮጲያ ኪነ ጥበብ በርካታ አስተዋጽኦ አድርገዋል። ተሳትፏቸውም ከፍ ያለ ነው።

አርቲስት ደበበ እናት ዓለም ጠኑ፣ የአዛውንቶች ክበብ፣ ኪንግ ሊር፣ ዋናው ተቆጣጣሪ፣ ዳንዴው ጨቡዴ፣ ያላቻ ጋብቻ፣ ናትናኤል ጠቢቡ፣ የቬኒሱ ነጋዴ፣ የከርሞ ሰው ከተወኑባቸው ቴአትሮች መካከል የሚጠቀሱ ሲሆን፤ 28 ተውኔቶችን አዘጋጅተው ለዕይታ አቅርበዋል።

በእንግሊዘኛ ከሠራቸው ፊልሞች መካከልም ‘ሻፍት ኢን አፍሪካ’ 'ዘ ሴይለር ፍሮም ጂብራልታር'፣ 'ጉማ'፣ 'ዘ አፍሪካን ስፓይ'፣ 'ዜልዳ'፣ 'ዘ ግሬቭ ዲገር' እና 'ዘ ግሬት ሪቤሊየን ' ይጠቀሳሉ።

በስነፅሁፍ ዘርፍም ከተዋናይ ሀሁ፤ የባሩድ በርሜል፤ድብልቅልቅ የመድረክ ተውኔት፣ ያልታመመው በሽተኛ፣ የደም እንባንና ሌሎችንም ሥራዎች ወደ አማረኛ ተርጉመዋል።

አርቲስት ደበበ እሸቱ የአፍሪካ መድረክ ባለሙያዎች ማህበር መሥራች ፣የዓለም ኮንቴምፖራሪ ቴአትር ኢንሳይክሎፒዲያ ቦርድ አባል፤ የዓለም አቀፍ ቴአትር ኢንስቲቲዩት የአፍሪካ አስተባባሪና የኢትዮጵያ ተጠሪ፤በብሔራዊ ቴያትር የፕሮግራምና ፕሮዳክሽን ኃላፊ፤በሀገር ፍቅር ቴአትር የኪነጥበብ አገልግሎትኃላፊና፣በራስ ቴአትር ዋና ሥራ አስኪያጅነት፣ በአትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን በርካታ ማህበራዊ፣ የልማትና እርዳታ አገልግሎቶችን ላይ አስተባባሪ፣ የሰላምና እርቅ ኮሚቴ አባል፣ የጌርጌሴኖን የአዕምሮ ህሙማን ማዕከል አምባሳደር፣ በኩላሊት ሞት ይብቃ አምባሳደር በመሆን አገልግለዋል። 

አርቲስት ደበበ እሸቱ ለአፍሪካ ቴአትር ባደረጉት አስተዋጽኦ የዚምባብዌን ማላካይት አዋርድ ተሸልመዋል፣ ጣይቱ ኢንተርቴንመንት በዋሽንግተን ዲሲ በቴአትር ዘርፍ የሕይወት ዘመን ተሸላሚ አድርጓቸዋል። በአትላንታ ጂኦርጂያ የከተማው ምክር ቤት ለዓለም ቴአትር ባደረጉት አስተዋጽኦ ኖቬምበር 24ን የደበበ እሸቱ ቀን በሚል ሰይሞላቸዋል።

የኢትዮጵያ ባህል ሚኒስትርም ለኢትዮጵያ ፊልም እድገት ላበረከቱት አስተዋጽኦ ሸልሟቸዋል። በጉማ አዋርድም የሕይወት ዘመን ተሸላሚ ሆነዋል። እ.አ.አ በ2015 በቫንኮቨር ዓለምአቀፍ ፊልም ፌስቲቫልም በምርጥ መሪ ተዋናይ ዘርፍ ተሸላሚ ሆነዋል። በ2015 ዓ.ም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለሀገራቸው ባበረከቱት አስተዋጽኦ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ አበርክቶላቸዋል።

አርቲስት ደበበ እሸቱ ከባለቤታቸው ወ/ሮ አልማዝ ደጀኔ ጋር በመሰረቱት የትዳር ሕይወታቸውም 4 ልጆችን አፍርተዋል።