በደቡብ ወሎ ዞን ተንታ ወረዳ በተከሰተ የናዳ አደጋ የ4 ሰዎች ሕይወት እንዳለፈ የተንታ ወረዳ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ወርቅነህ መላኩ ለኢቢሲ ዶትስትሪም ገለጸዋል።
በተንታ ወረዳ 01 ያመድ ቀበሌ ልዩ ሥሙ "ሳሬታ" በተባለ ቦታ ነሃሴ 10/2017 ዓ.ም ምሽት ላይ በደረሰ የናዳ አደጋ ምክንያት፤ የቤት እንሰሳትን ጨምሮ የአንድ አርሶ አደር ቤተሰብ አባላት ሕይወታቸው ማለፉን ገልጸዋል።
በደረሰዉ የናዳ አደጋ ትልቅ ቋጥኝ የቆርቆሮ ክዳን ባለው መኖሪያ ቤት ላይ በማረፉ ቤቱ ውስጥ የነበሩ አራት ሰዎች የቤት እንሰሳት እንዲሁም ሣር ቤቱ በአደጋው እንደወደመም ኃላፊው አንስተዋል።
እስካሁን ከአደጋው አንድ አስከሬን ብቻ ማውጣት የተቻለ ሲሆን፤ የሌሎቹን 3 ሰዎች አስከሬን ለማውጣት የአካባቢው ማህበረሰብ ርብርብ በማድረግ ላይ መሆኑንም ነው የተናገሩት።
ቤቱ ላይ ያረፈው ቋጥኝ ድንጋይ ከባድ በመሆኑ አስከሬኖችን ለማውጣት የሚደረገውን ጥረት አስቸጋሪ አድርጎታልም ብለዋል ኃላፊው።
በቢታኒያ ሲሳይ