የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር በአርቲስት ደበበ እሸቱ ህልፈተ ሕይወት የተሰማውን ሀዘን ገልጿል።
የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሀዘን መግለጫ እንደሚከተለው ቀርቧል:-
በኢትዮጵያ የኪነ ጥበብ ታሪክ ውስጥ ጉልህ ሚና ከተጫወቱ አንዱና ግንባር ቀደሙ አንጋፋው የመድረክ ፈርጥ፣ ደራሲ፣ ተርጓሚ፣ ተዋናይ፣ ከያኒ፣ ጋዜጠኛ፣ የመብት ተሟጋች እና ሀገር ወዳዱ የክብር ዶክተር አርቲስት ደበበ እሸቱ ነሐሴ 11/ 2017ዓ.ም በ83 ዓመታቸው ባደረባቸው ህመም ምክንያት በህክምና ሲረዱ ቆይተው ከዚህ ዓለም ድካም ማረፋቸውን በመስማታችን ታላቅ ሀዘን ተሰምቶናል።
ከያኒው በዘመናቸው የኢትዮጵያ የምንጊዜም ታማኝ አገልጋይ ለህዝባቸውና ለአገራቸው ጥቅም የኖሩ ጎምቱ የጥበብ ሰው ነበሩ።
የክብር ዶክተር ደበበ እሸቱ በደራሲነት፣ በተዋናይነት፣ በአዘጋጅነት፣ በቴአትር አስተዳደር እና የማኅበር መሪነት በሀገር ውስጥ፣ በአፍሪካ እና በአለም መድረክ ኢትዮጵያን ያገለገሉ ቀዳሚ ከያኒ ነበሩ። አበርክቶ ካደረጉባቸው ሥራዎች የሚከተሉት ይጠቀሳሉ። ያላቻ ጋብቻ፣ ሮሚዎና ዡልየት፣ ጠልፎ በኪሴ፣ ዳንዴው ጨቡዴ፣ አዳ ኦክ ኦራክል፣ የበጋ ሌሊት ራዕይ፣ እናት ዓለም ጠኑ፣ ኪንግ ሊር፣ የአዘውንቶች ክበብ፣ የቬኒሱ ነጋዴ፣ ናትናኤል ጠቢቡ ድብልቅልቅ፣ ዘ ሴይለር ፍሮም ጂብራልታር፣ ሻፍት ኢን አፍሪካ፣ ጉማ፣ የደም እምባ፣ የእምነቴ ፈተና ይጠቀሳሉ።
ክቡር ዶክተር ደበበ እሸቱ በታንዛኒያ፤ ኡጋንዳ፤ ኬንያ፤ ማላዊ፤ ኮንጎ ብራዛቪል፤ አይቮሪ ኮስት፤ ካሜሩን፤ ናይጄርያ፤ አይርላንድ፤ ብራዚል፤ ሰሜን አሜሪካ፤ እንግሊዝ፤ ኩባ፤ በርሊን፤ ካናዳ በመዘዋወር ለሞያቸው እና ለሀገራቸው ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርገዋል።
ከያንያን የሀገር ፍቅር ተላብሰው ለሀገራቸው መቆም እንደሚኖርባቸው በሞያቸው እና በሕይወታቸ ግምባር ቀደም ምሳሌነት ባለው ጽናት ኢትዮጵያ ሀገራቸውን አገልግለው በማለፋቸው የተሰማን ሀዘን ጥልቅ ነው።
ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ለቤተሰቦቻቸው፣ ለጓደኞቻቸው ለዘመዶቻቸው እና ለአድናቂዎቻቸው መጽናናትን ይመኛል።