በአንድ ጀምበር፣ በተወሰኑ የብርሃን ሰዓታት ውስጥ፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ እጆች ለአንዲት ሀገር የጋራ ዓላማ ሲሰባሰቡ ማየት እጅግ አስደናቂ ሀገራዊ ተዓምር ነው።
በኢትዮጵያ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ታሪክ ውስጥ "አንድ ጀምበር" የሚለው ቃል ትርጉሙ እጅግ ጥልቅ፣ መንፈሱም እጅግ ረቂቅ ነው።
ይህ ቀን ኢትዮጵያውያን እጅ ለእጅ ተያይዘው በተፈጥሮ ላይ የጋራ ዐሻራቸውን የሚያኖሩበት ልዩ የታሪክ መድረክ ነው።
ባለፉት ዘመናት የሀገራችን ታሪክ ውስጥ፣ የኢትዮጵያን ሕዝብ ልክ እንደ አረንጓዴ ዐሻራ በአንድ ልብ ያሰባሰበው እና በጋራ ስሜት አንድ ያደረገው ሀገራዊ አጀንዳ የለም ቢባል ማጋነን አይሆንም።
ይህንን የማይካድ እውነት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድም በተደጋጋሚ አረጋግጠውታል። አረንጓዴ ዐሻራ ከተራ የፖለቲካ ትርክት፣ ከብሔር እና ከሃይማኖት ልዩነቶች በላይ ከፍ ብሎ፣ ሕዝብን በጋራ የብልጽግና ራዕይ ያስተሣሠረ የዘመናችን ታላቅ የትብብር እና የመደመር ማሳያ ነው።
ባለፉት ጥቂት የለውጥ ዓመታት በአንድ ጀምበር የተመዘገቡት የችግኝ ተከላ ስኬቶች፣ የዚህን አብዮት ጉልበት እና ዕድገት በግልጽ ያሳያሉ። የነገዋን ኢትዮጵያ በምናብ ሥሎ የተነሣው ይህ ትውልድ፣ በአንድ ጀምበር 80 ሚሊዮን ችግኞችን የመትከልን ዕቅድ እንደ ትልቅ የስኬት ማማ ተመልክቶት ነበር።
ነገር ግን የሕዝቡ የጋለ ተነሣሽነት ከተቀመጠው የዕቅድ ጣሪያ እጅግ የላቀ ሆኖ ተገኝቷል። እ.አ.አ. በ2019 በአንድ ቀን ከ353 ሚሊዮን በላይ ችግኞች በመትከል የዓለምን ክብረ ወሰን የሰበረችው ኢትዮጵያ፣ ይህንን ሪከርድ በማሻሻል በ2021 በአንድ ጀምበር ከ400 ሚሊዮን በላይ ዐሻራዎችን አሳረፈች።
ይህ የአንድ ጀምበር ገድል በከፍተኛ የሕዝብ ንቅናቄ እያደገ መጥቶ፣ በ2023 በአንድ ጀምበር ከ566 ሚሊዮን በላይ፣ እንዲሁም በ2024 በአንድ ቀን ከ600 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል የዓለምን ማኅበረሰብ ያስደመመ ሀገራዊ አቅም መፍጠር ችላለች። በ2025 ደግሞ ከ714 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን በአንድ ጀምበር በመትከል "ይህ አይቻልም" የተባለውን የአቅም ጣሪያ ሰብራለች።
ይህ የአንድ ጀምበር ተዓምር፣ ከደረቅ የቁጥር ስሌት አልፎ ምድሪቱን በተግባር እያለማት እና እየቀየራት ይገኛል። የተተከሉት ችግኞች ጸድቀው የከርሰ ምድር ውኃ መጠን በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጨምር፣ የዝናብ ሥርጭት መደበኛነቱን እንዲጠብቅ እና የተፈጥሮ ሚዛን በአዲስ መልክ እንዲስተካከል ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው። ቀደም ሲል በድርቅ የተመቱ እና የተራቆቱ አውራጃዎች ዳግም አረንጓዴ ልብሳቸውን ለብሰዋል፤ የደረቁ ምንጮች ዳግም ፈልቀዋል፤ የተረሳው የተፈጥሮ ውበትም ወደ ቀያችን ተመልሷል።
ከዚህም ባሻገር፣ አረንጓዴ ዐሻራ ለታላላቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ሕልውና እጅግ ወሳኝ የጀርባ አጥንት ሆኗል። የኢትዮጵያውያን የላብ ፍሬ የሆነው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ በደለል አደጋ እንዳይሞላ እና ውኃን በአግባቡ የመያዝ አቅሙ እንዳይቀንስ፣ ግድቡን የሚያዋስኑ ግዙፍ ተፋሰሶችን በደን የመሸፈን ሥራ በስኬት ተከናውኗል። ይህ የደን ልማት ደግሞ የግብርና ምርታማነትን በከፍተኛ ደረጃ በማሳደግ፣ ሀገራችን በምግብ ራስን ወደ መቻል ለምታደርገው የብልጽግና ጉዞ ጠንካራ መሠረት ጥሏል።
የኢትዮጵያ አረንጓዴ ዐሻራ ስኬት እና የለውጥ ሞገድ በሀገር ውስጥ ድንበር ብቻ የተገደበ አይደለም። ኢትዮጵያ እየሠራችው ያለው ተዓምር ድንበር ተሻግሮ፣ ጎረቤት ሀገራትም የዚህ የአረንጓዴ ተጽዕኖ (Green Effect) ቀጥተኛ ተካፋይ እንዲሆኑ አድርጓል።
ኢትዮጵያ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የችግኝ ስጦታዎችን ለጎረቤት ሀገራት በልግስና በማበርከት፣ የቀጣናውን የአየር ንብረት ለውጥ በጋራ ለመቋቋም የሚያስችል ጠንካራ መሠረት እየጣለች ነው።
በዚህም ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ዲፕሎማሲ ውስጥ ያላትን የ"ግሎባል ሳውዝ" የመሪነት ሚና በተግባር እያረጋገጠች ትገኛለች።
በአጠቃላይ፣ የአንድ ጀምበር ተዓምር የኢትዮጵያውያን የጋራ አቅም፣ የአንድነት ኃይል እና የጽናት ማሳያ ነው። ይህ ትውልድ በገዛ እጁ አፈሩን እያለሰለሰ፣ በላቡ እያጠጣ ያሳደጋቸው እነዚህ ታሪካዊ ችግኞች፣ የነገዋን የዳበረች፣ የለመለመች እና በሁለንተናዊ ብልጽግና የተንቆጠቆጠች ኢትዮጵያን ብሩህ ተስፋ የሚያበስሩ ሕያው ምስክሮች ናቸው።
ይህ በአንድ ጀምበር የተዘራው 800 ሚሊዮን የተስፋ ዘር፣ አዲሲቷ ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ጸጋዋ ዳግም ለዓለም የምትተርፍበትን ብሩህ ዘመን አብስሯል!
በአዶኒያስ ወልደአረጋይ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: