በ2018 የበጀት ዓመት 607 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የሚያወጣ ምርት ለውጭ ገበያ ማቅረብ መቻሉን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታውቋል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል በመድረኩ ላይ እንደገለጹት፤ መንግሥት ለማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ በሰጠው ልዩ ትኩረት እና በ”ኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ አማካኝነት በዘርፉ አመርቂ ውጤቶች እየተመዘገቡ ይገኛሉ፡፡ በዚህም ከፍተኛ የሥራ ዕድል የመፍጠር እና የሀገር ውስጥ ምርትን የማሳደግ አቅም እየጎለበተ መምጣቱን አንስተዋል።
በዘርፉ ከተመዘገቡት ዐበይት ለውጦች መካከል በዓመት ወደ ማምረት የሚገቡ አዳዲስ ኢንዱስትሪዎች ቁጥር ከ2 ሺህ 787 ወደ 4 ሺህ 587 ያደገ ሲሆን፣ የኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም አጠቃቀም ከ47 በመቶ ወደ 59.3 በመቶ ከፍ ብሏል።
በተጨማሪም በ2018 የበጀት ዓመት 5.9 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ የገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት መተካት መቻሉን ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡ በ2019 የበጀት ዓመት ደግሞ የኤክስፖርት ገቢውን ወደ 1 ቢሊዮን ዶላር ለማድረስ ታቅዶ እየተሠራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
ለአምራች ኢንዱስትሪው የሚደረገው ድጋፍም እያደገ መምጣቱ የተገለጸ ሲሆን፣ ለዘርፉ የሚቀርበው የብድር መጠን ቀደም ሲል ከነበረበት 40 ቢሊዮን ብር በአሁኑ ወቅት ከ115 ቢሊዮን ብር በላይ አድጓል።
ከዚህ በተጨማሪም ለአምራች ኢንዱስትሪው ይቀርብ የነበረው የውጭ ምንዛሬ ከ450 ሚሊዮን ዶላር ወደ 1 ቢሊዮን ዶላር ከፍ እንዲል ተደርጓል። በቀደምት ጊዜያት በዓመት ይፈጠር የነበረው 162 ሺህ የሥራ ዕድልም አሁን ላይ ከ430 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ተደራሽ ማድረግ ተችሏል።
በዘርፉ ያሉ በርካታ ተደራራቢ ፈተናዎችን አልፈው በበጀት ዓመቱ በኤክስፖርት ዘርፍ ላቅ ያለ አፈጻጸም ላስመዘገቡ የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች እንዲሁም ተቋማት ዕውቅና ተሰጥቷል።
በብሩክታዊት አስራት
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: