Search

የአረንጓዴ ተዓምር ኢኮኖሚያዊ ዕይታ

ረቡዕ ሐምሌ 22, 2018 44

በኢትዮጵያ ውስጥ በስፋት እየተተገበረ ያለው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የተፈጥሮን ሚዛን ከመጠበቅ ባለፈ፣ የኢትዮጵያን የማክሮ ኢኮኖሚ መዋቅር ከሥር መሠረቱ እያደሰ እና እየገነባ ያለ ግዙፍ የፋይናንስ ሞተር ሆኗል።

ይህ ንቅናቄ ዛፍ ከመትከል የዘለለ እጅግ ጥልቅ ትርጉም ያለው ሲሆን፣ "ከጥላ ማግኘት ወደ ኪስ ማዳበር" "ከጓሮ ውበት ወደ ማዕድ መሙላት" እንዲሁም "ከአካባቢ ጥበቃ ወደ አግሮ-ኢንዱስትሪ ትሥሥር" የተደረገ ታላቅ የኢኮኖሚ ሽግግር በውስጡ ያዘለ ነው።

የዚህ አብዮት ትሩፋት ዛሬ ላይ እስከ እያንዳንዱ ዜጋ የዕለት ተዕለት ኑሮ እና ኪስ ድረስ ዘልቆ በመግባት ተጨባጭ የኢኮኖሚ ፋይዳ እያመጣ ይገኛል።

የዚህ ሰንሰለት መነሻ የተፈጥሮ ሥነ ምኅዳርን ማስተካከል ነው። የተራቆቱ መሬቶችን መልሶ በደን በማልበስ የአፈር መሸርሸርን መከላከል እና የተፈጥሮ እርጥበትን መጠበቅ የምግብ ዋስትናን በተግባር ለማረጋገጥ ወሳኝ ሚና ተጫውቷል።

ይህ የተፈጥሮ ሚዛን መጠበቅ በቀጥታ ወደ ግብርና ምርታማነት ዕድገት ተተርጉሟል። ለምሳሌ፣ ከሰባት ዓመታት በፊት ወደ ውጭ ይላክ የነበረው 230 ሺህ ቶን የቡና ምርት፣ በአረንጓዴ ዐሻራ በተሠራው ጠንካራ ሥራ በአሁኑ ወቅት ወደ 475 ሺህ ቶን በማደግ ሀገራችን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እንድታገኝ አስችሏል።

አሁን ላይ የዘመኑ ኢኮኖሚ የአካባቢ ጥበቃን ያማከሉ ተፈጥሮአዊ ምርቶችን በከፍተኛ ዋጋ የሚገዛ ሲሆን፣ አረንጓዴ ዐሻራም ኢትዮጵያን የዚህ ዓለም አቀፍ የጥራት መስፈርት ተወዳዳሪ አድርጓታል።

የምርታማነት ዕድገት ወደ ዜጎች ተጠቃሚነት ሲወርድ አስደናቂ ለውጥ አምጥቷል። አነስተኛ አርሶ አደሮች ለቤት ማገዶ ብቻ የሚውሉ ባሕላዊ ዛፎችን በመተው፣ በዓለም ገበያ ተፈላጊ በሆኑ እንደ አቮካዶ፣ ማንጎ እና ፓፓያ ባሉ የፍራፍሬ ዛፎች ተክተዋቸዋል።

እነዚህ ምርቶች በኢትዮ-ጂቡቲ የባቡር መስመር በማቀዝቀዣ ኮንቴይነሮች ወደ አውሮፓ እና መካከለኛው ምሥራቅ በመላክ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እያስገኙ ነው።

በሌላ በኩል ዘርፉ ግዙፍ የእሴት ሰንሰለት በመፍጠር፣ 120 ሺህ በላይ የችግኝ ጣቢያዎችን በማንቀሳቀስ በመቶ ሺዎች ለሚቆጠሩ ወጣቶች እና ሴቶች የገቢ ምንጭ ሆኗል።

"ኤፍ ኤስ አፍሪካ" የተሰኘው ተቋም እንዳረጋገጠው፣ የግብርና እና የተፈጥሮ ጥበቃ ውህደት በኢትዮጵያ እስከ 700 ሺህ የሚደርሱ አዳዲስ የሥራ ዕድሎችን የመፍጠር አቅም አለው።

በማክሮ ኢኮኖሚው ደረጃ፣ አረንጓዴ ዐሻራ ለግብርና-ኢንዱስትሪ ፓርኮች የጀርባ አጥንት ሆኗል። በይርጋለም፣ ቡሬ እና ኮምቦልቻ ለተቋቋሙ የፍራፍሬ ጭማቂ ማቀነባበሪያዎች የጥሬ ዕቃ በማቅረብ ከውጭ ይገባ የነበረውን ግብዓት ተክቷል።

በተጨማሪም፣ በዓባይ ተፋሰስ የተተከሉት ደኖች የታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ከደለል በመታደግ የኢትዮጵያን የውኃ እና የኃይል ዋስትና አረጋግጠዋል።

እንደ እንጦጦ እና ወዳጅነት መናፈሻ ያሉት ፕሮጀክቶችም አዲስ የቱሪዝም ገቢ እና የሪል እስቴት እሴት መጨመርን አምጥተዋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ አረንጓዴነት ከፍተኛ ዋጋ ይሰጠዋል። ኮስታሪካ ከኢኮ-ቱሪዝምና ከካርቦን ክሬዲት ክፍያ በቢሊዮን ዶላሮች እንደምታገኘው፣ እና ደቡብ ኮሪያ የእንጨት ምርት ገቢዋን እንዳሳደገችው ሁሉ፣ ኢትዮጵያም 50 ቢሊዮን ችግኞችን በመትከል በአፍሪካ ቀንድ ትልቁን የካርቦን ማከማቻ ለመቆጣጠር አልማለች።

ባለፉት ዓመታት የተተከሉት 48 ቢሊዮን በላይ ችግኞች የደን ሽፋኑን ወደ 23 ነጥብ 6 በመቶ አሳድገውታል። አረንጓዴ ዐሻራ ከችግኝ ማፍላት እስከ ዓለም አቀፍ የካርቦን ገበያ የተዘረጋ፣ ተፈጥሮን በማደስ የማክሮ ኢኮኖሚ ፋይዳዎችን በማምጣት የእያንዳንዱን ዜጋ ማዕድ የሚሞላና ኪስ የሚያዳብር የሕልውና ዋስትና መሆኑን በተግባር እያረጋገጠ ነው።

በአዶኒያስ ወልደአረጋይ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: