ሀገራዊ ምክክሩ ለረጅም ዘመናት ሲንከባለሉ የነበሩ የሐሳብ ልዩነቶችን በጠረጴዛ ዙሪያ የምንፈታበት እና የኢትዮጵያን መፃዒ ዕድል የምንወስንበት ታሪካዊ ጉባኤ ነው ሲሉ የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዎች ተናግረዋል።
ምክክር የሐሳብ የበላይነትን የሚያስቀድም የእኔ ብቻ ይሁን ከሚል አስተሳሰብ እና አመለካከት ወጥተን እኛ የሚለውን የጋራ እሳቤ የሚያስቀድም የልዩነቶቻችን መሻሪያ ቁልፍ መሣሪያ መሆኑን ነው ነዋሪዎቹ የገለጹት።
ከዚህ በፊት ባለመማካከራችን ብዙ ነገር አጥተናል፣ ተጎድተናል፤ አሁን ላይ ግን በታሪክ አጋጣሚ የተገኘውን ዕድል አሟጥጦ መጠቀም ይገባል ብለዋል።
በምክክር ጉባኤውም ከዚህ በፊት በአጀንዳ ማሰባሰብ ምዕራፉ ያነሧቸውን፦ የሰላም ጉዳይ፣ የወሰንና የማንነት ጉዳይ፣ የአዲስ አበባ ጉዳይ፣ የሰንደቅ ዓላማ ጉዳይ እና ሌሎች አጀንዳዎች ላይ የጋራ ተግባቦት ይፈጠራል ብለው በጉጉት እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።
በምክክሩ ከመላው ኢትዮጵያ የተወጣጡ ከ4000 በላይ ተመካካሪዎች በጋራ መምከራቸው ኢትዮጵያን ወደ ላቀ ልዕልና ለማሻገር የሚደረግ ጥረት መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም ኢትዮጵያውያን በራሳቸው አቅም ሀገራዊ ችግሮቻቸውን በጠረጴዛ ዙሪያ የመፍታት አቅማቸውን ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ያሳዩበት በጎ ጅማሮ ነው ብለዋል።
ወጣቱ ትውልድም ሰክኖ እና ራሱን ከተሳሳቱ ዝንባሌዎች አርሞ በታሪክ አጋጣሚ የተገኘውን ዕድል ሊጠቀም እንደሚገባም ነዋሪዎቹ አሳስበዋል።
ኢትዮጵያውያን አሁን ላይ እንደ ሀገር እየታየ ያለውን የአንድነት የብርሃን ጮራ የበለጠ በማጉላት እንዲሁም ገዥ ትርክቶችን በመትከል ከውስጥ እና ከውጭ የሚቃጡብንን የጠላት ሴራዎች በማክሸፍ የጋራ ጥቅሞቻችንን ማስከበር እንደሚገባም ጠቁመዋል።
ለምክክሩ ስኬትም ኢትዮጵያዊ የሆነ ሁሉ የበኩሉን ሚና እንዲጫወት ጥሪ አቅርበዋል።
በተስፋሁን ደስታ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: