የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ በ2018 የሥራ ዘመን ከ1.4 ትሪሊዮን ብር በላይ (9.1 ቢሊዮን ዶላር) ገቢ ማግኘቱን ይፋ አደረገ።
የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው የአየር መንገዱን የ2018 በጀት ዓመት አጠቃላይ የሥራ አፈጻጸም አስመልክተው በሰጡት መግለጫ እንደገለጹት፣ ዘንድሮ የተመዘገበው ገቢ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ20 በመቶ ዕድገት ያሳየ ነው።
ዋና ሥራ አስፈጻሚው አያይዘውም፣ የበጀት ዓመቱ በልዩ ልዩ የተቋሙ የሥራ እንቅስቃሴዎች ውጤታማ ተግባራት የተከናወኑበት እንደነበር ጠቁመዋል።
በዚሁ መሠረት አየር መንገዱ በዓመቱ 4 አዳዲስ የዓለም አቀፍ የበረራ መስመሮችን በመክፈት አጠቃላይ የዓለም አቀፍ መዳረሻዎቹን ቁጥር ወደ 150 ማድረስ ችሏል።
በተጨማሪም የ3 አዳዲስ የሀገር ውስጥ መዳረሻዎችን ግንባታ በማጠናቀቅ የሀገር ውስጥ የበረራ አውታሩን ከ22 ወደ 25 ማሳደጉ ተገልጿል።
በዚሁ ዓመት አየር መንገዱ በአጠቃላይ 20.7 ሚሊዮን መንገደኞችን ሟጓጓዙ ተጠቁሟል።
በሌላ በኩል፣ የበጀት ዓመቱ ስኬታማ እንቅስቃሴዎች የታዩበት ቢሆንም ተቋሙ ከፍተኛ ፈተናዎች እንዳጋጠሙት ተጠቅሷል።
በተለይም በመካከለኛው ምስራቅ በተከሰተው አለመረጋጋት ምክንያት ያጋጠመው የነዳጅ አቅርቦት እጥረት የአየር መንገዱን የሥራ እንቅስቃሴ በእጅጉ ፈትኖት ማለፉን አቶ መስፍን በመግለጫቸው አስረድተዋል።
በአሚር ጌቱ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: