በአሜሪካ መንግሥት የመካከለኛው ምሥራቅ እና አፍሪካ ምክትል ረዳት ሚኒስትር ማርክ ሚሼል የተመራ ከፍተኛ ልዑክ በኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት የሥራ ጉብኝት አድርጓል።
በጉብኝቱ ወቅት የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር) ለልዑካን ቡድኑ ባደረጉት ገለጻ፣ በኢትዮጵያ እና በአሜሪካ መካከል ያለውን የረጅም ዓመታት ታሪካዊ ግንኙነት በማስታወስ፣ ኢንስቲትዩቱ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዘርፍ የሚያከናውናቸውን ዋና ዋና ተግባራት በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ በገለጻቸው ኢንስቲትዩቱ በሰው ሠራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ ምርምር እና ልማት ስኬታማ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን አስተረድተዋል።
በተለይም በተፈጥሮ ቋንቋ ቅንብር የኢትዮጵያን ሀገር በቀል ቋንቋዎች ለማሽን በማስተማር ረገድ ሀገራችን ለልዩ ልዩ ተግባራት መጠቀም መጀመሯን አስረድተዋል።
በተጨማሪም ስታርታፖችን ለመደገፍ ኢትዮጵያ በልዩ ትኩረት እሠራች እንደሆነ እና በትብብር አብሮ ለመሥራት ምቹ ምኅዳር መኖሩን ገለጸዋል።
በአሜሪካ መንግሥት የመካከለኛው ምሥራቅ እና አፍሪካ ምክትል ረዳት ሚኒስትር ማርክ ሚሼል በበኩላቸው፣ ለተደረገላቸው አቀባበል እና ገለጻ ምስጋና አቅርበው የኢንስቲትዩቱ እንቅስቃሴ ከጠበቁት በላይ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢንስቲትዩቱ ለስታርታፖች የሰጠውን ከፍተኛ ትኩረት እና የሚያደርገውን ድጋፍ ያደነቁት ሚኒስትሩ በሮቦቲክስ፣ በሆሎግራም ቴክኖሎጂ፣ በተፈጥሮ ቋንቋ ቅንብር እና በሌሎችም ዘርፎች ያከናወናቸው ተግባራት ለአርአያነት የሚበቁ ናቸው ብለዋል።
ከጉብኝቱ ጎን ለጎንም ሁለቱ ሀገራት በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂ ዘርፍ በጋራ መሥራት በሚችሉባቸው ሁኔታዎች ላይ ፍሬያማ ውይይት ማካሄዳቸውን ከኢንስቲትዩቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: