Search

ዘመን ወደኋላ አይቆጥርም፤ ትውልድም አይሸነፍም!

ሓሙስ ሐምሌ 23, 2018 63

ሐሳብ ይወለዳል፣ ያድጋል፣ ጥቅም ላይ ይውላል፣ ያረጃልም። ይህ የተፈጥሮ ዑደት ነው። በእርግጥ ዘመናትን የሚሻገሩ፣ የማያረጁ እና ሁልጊዜም ብሩህ ሆነው የሚኖሩ ጥልቅ ሐሳቦች አሉ። በተቃራኒው ደግሞ አንዳንዶቹ ሐሳቦች ገና ከጅምሩ ሲወለዱም የጨነገፉ ሆነው ይወለዳሉ።

ከዓለም ፍጥረት አንስቶ ጊዜ እና ዘመን ወደፊት ይገሰግሳል እንጂ፣ ለአፍታም ቢሆን ቆሞ አያውቅም፤ ፈጽሞም ወደኋላ ሊቆጥር አይችልም። ማንም ሰው ቢመኝ እና ቢጓጓ ወደነበረበት የልጅነት ዘመኑ መመለስ እንደማይችለው ሁሉ፣ ከዘመን ጋር መጣላትም ሆነ ታሪክን ወደኋላ መመለስ አይቻልም። በአረጀ አቁማዳ አዲስ የወይን ጠጅ ማጠራቀም አይቻልም፤ አዲሱ ወይን ያረጀውን አቁማዳ ቀዶት ይፈሳልና። ያለፉ ትውልዶች እና ያረጁ ሐሳቦች ለጊዜው አጃቢ አግኝተው ጭብጨባ ቢቸራቸውም፣ የዘመኑን እውነት የታጠቀው አዲሱ ትውልድ እና አዲስ ሐሳብ ግን ውሎ አድሮ ማሸነፋቸው የማይቀር ተፈጥሯዊ ሀቅ ነው።

ህገወጡ የህወሓት ቡድን ግን፣ ከዚህ የተፈጥሮ እና የዘመን ህግ በተቃራኒ የሚቆም፣ እውነታውን የካደ ስብስብ ነው። ከግማሽ ፍለ ዘመን ጀምሮ የያዘውን እና ገና ሲወለድ የጨነገፈውን የጥፋት እሳቤ፣ ዛሬም በዚህ አዲስ የዕውቀት ዘመን አዲሱን ትውልድ ሊያሞኝበት እና ሊያታልልበት ይሞክራል። ከተፈጠረበት ጊዜ አንስቶ ይዞ ባመጣው ሐሳብ ላይ ምንም ዓይነት የሐሳብ ለውጥ፣ ማሻሻያም ሆነ የእድገት እርምጃ ማድረግ የማይችል ነው።

አንድ ጊዜ  የገለበጠውን የሶሻሊስት ማኒፌስቶ ከትውልድ ወደ ትውልድ እያቀባበለ፣ ያንኑ ያረጀ የጥፋት ዜማ ከዘመን ዘመን እየደገመ የሚኖር የቅራኔ ስብስብ ነው። በየትኛውም ዘመን ቢሆን ከጠላት እና ወዳጅ የፈጠራ ትርክት ውጭ መቆም አይችልም። ሁልጊዜም ስጋትን፣ ግጭትን እና ደም መፋሰስን እንደ ዕድሜ ማራዘሚያ እና የኅልውና መቀጠያ አድርጎ የሚጠቀም፣ ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ አንዲትም ስንዝር አዲስ ሐሳብ ያላሳደገ አፍራሽ ኃይል ነው።

ይህ ህገወጥ ቡድን የትግራይን ሕዝብ በጠላት እንደተከበበ  አድርጎ በመሳል፣ "ተከበናል፤ ሁሉም ይጠላናል" በሚል የሀሰት ትርክት ጨምድዶ ለመግዛት የሚጥር፣ በልዩነትና ግጭት መሀል ትርፍ ለማስላት የሚሞክር አቅመ-ቢስ ነው።

ዛሬ ላይ ከ50 ዓመታት በኋላ፣ ዓለም በሥልጣኔ፣ በቴክኖሎጂ እና በእውቀት ማማ ላይ በደረሰችበት በዚህ ዘመን፣ ይህ ቡድን ያንን ያረጀ እና የሻገተ ዜማውን ይዞ የዛሬውን ንቁ ትውልድ እገዛለሁ ብሎ ማሰብ፣ እጅግ ቀልበ-ቢስ እና በከፍተኛ የቅዠት ዓለም ውስጥ የሚኖር መሆኑን ያረጋግጣል።

የዚህ የጥፋት ዜማ ቁልፍ ማሳያዎች እጅግ ግልጽ እና ደጋግመው የሚታዩ ናቸው። ዘወትር ጠላትን መፍጠር እና በማያባራ የጦርነት አዙሪት ውስጥ ራሱን እንደ ብቸኛ "አዳኝ" እና "መልአክ" አድርጎ ለማቅረብ ይሞክራል።

የትግራይን ሕዝብ መከታ አድርጎ በየመግለጫዎቹ ሌላውን ፋሺስት፣ አምባገነን እና ጨፍጫፊ እያለ ቢከስም፤ ከዚህ ሁሉ የውሸት ጭንብል ጀርባ ያለው እውነተኛ ማንነቱ ግን፣ በሕዝብ ስጋትና ሰቆቃ ውስጥ የራሱን ጠባብ የቡድን ጥቅም ማስጠበቅ፣ ግላዊ ፍላጎቱን ማርካት እና ሀብት መዝረፍ ብቻ ነው።

ለ50 ዓመታት ያልተቀየረው ሌላው የክፋት መገለጫው፣ ራሱንና የትግራይን ሕዝብ አጣብቆ ለማቅረብ የሚያደርገው እኩይ ጥረት ነው። "እኔን የነካ የትግራይን ሕዝብ ነካ" በሚል  ማታለል፣ ለዘረፈው ሀብት፣ ለፈጸመው ወንጀል እና ለገባበት ታሪካዊ ዕዳ ሕዝቡ ተካፋይ እንዲሆን ያላክካል። ይህ ድርጊቱ፣ ቡድኑ ለትግራይ ሕዝብ ያለውን ጥልቅ ጥላቻ፣ ንቀት እና እኩይነት በተግባር የሚያሳይ ነው። ይህ ስብስብ ቋሚ መርህ የሌለው፣ አንደበቱ እና ተግባሩ የማይገናኝ ሙሉጭልጭ ነው። በአንድ በኩል ድሃውን የትግራይ ወጣት "ተዋጋልኝ፣ ተሰለፍልኝ" እያለ በአቋራጭ ወደ እሳት ይማግዳል፤ በሌላ በኩል ደግሞ የሕዝቡን አንጡራ ሀብት በኮንትሮባንድ እያሸሸ ካዝናውን ያደልባል።

አሁን ግን ጊዜው ተቀይሯል። የትግራይ ሕዝብም ሆነ ወጣቱ የቡድኑን እኩይነት ሙሉ በሙሉ ተረድቶ፣ ከሌላው ኢትዮጵያዊ ወንድሙ ጋር በመተባበር ይህንን ዘመን ያለፈበትን የጥፋት ተሽከርካሪ ከጫንቃው ላይ እያወረደው ይገኛል። አዲሱ ትውልድ በሀሰተኛ ትርክት የሚሸነፍበት ዘመን አብቅቷል። የትግራይ ወጣት የቡድኑ ማታለያ ለዘለዓለም እንዲያበቃ ቆርጦ ተነስቷል፤ ምክንያቱም የትውልድ ዘመን ወደኋላ አይቆጥርም፤ ትውልድም ፈጽሞ አይሸነፍም!

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: