በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ በርካቶች "የነጻ አውጪነትን" ካባ ደርበው ብቅ ቢሉም፣ እውነተኛ ዓላማቸው ግን ፖለቲካን እንደ አዋጭ የንግድ ገበያ መጠቀም ነው። በዚህ የረከሰ የፖለቲካ ገበያ ውስጥ መርህ ቦታ የለውም። ርዕዮተ-ዓለምም የጥቅም ማስከበሪያ ጭንብል ብቻ ነው።
የፖለቲካ ንግዱ ዋና ማጠንጠኛ ሕዝብን እንደ ሸቀጥ በመቁጠር፣ በስጋት እና በግጭት ውስጥ የግል እና የቡድን ካዝናን ማደለብ ነው። በዚህ ገበያ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ቡድኖች ሀገርን እና ሕዝብን የሚመለከቱት እንደ መበዝበዣ ፕሮጀክት እና የትርፍ ምንጭ አድርገው ነው።
ከዚህ አስነዋሪ የፖለቲካ የንግድ ስሌት አብራክ የወጣው እና ዘመናትን የተሻገረው ህገ-ወጡ የህወሓት ቡድን፣ የዚህ የዝርፊያ እና የህገ-ወጥነት ጉዞ ዋነኛ ተምሳሌት ነው። ይህ ስብስብ ከተፈጠረበት ጊዜ አንስቶ ፖለቲካን የሕዝብ ማገልገያ ሳይሆን፣ ያለአንዳች ከልካይ ሀብት የሚያካብትበት የኮንትሮባንድ መስመር አድርጎት ኖሯል።
"እታገልለታለሁ" የሚለውን የትግራይን ሕዝብ ስም እንደ ንግድ ፈቃድ በመጠቀም፣ በሕዝቡ ስቃይ እና ደም ላይ ቆሞ የራሱን ቋት ሲያደልብ የኖረ የጥፋት ነጋዴ ነው። ለዚህ ቡድን የፖለቲካ ትግል ማለት፣ ሥልጣንን ተጠቅሞ የሕዝብን ደም የመምጠጥ እና በሀገር ሀብት የመክበር ህጋዊ ያልሆነ ስምምነት ነው።
የዚህ ህገ-ወጥ ቡድን የዕለት ተዕለት ተግባር ከፖለቲካ ፓርቲነት ባህሪ ጋር ፈጽሞ አይገናኝም። ይልቁንም በተደራጁ እና ዓለም አቀፍ የዝርፊያ መረብ (Cartel) ውስጥ በሚታዩ አስነዋሪ ወንጀሎች ላይ የተመሰረተ ነው። ዋነኛ የገቢ ምንጩም በህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር (Human Trafficking) እና የተፈጥሮ ሀብት ኮንትሮባንድ ላይ የተንጠለጠለ ነው። የትግራይን ወጣት በማታለልም ሆነ በማስገደድ ለውጭ ኃይሎች በቅጥር ወታደርነት በመሸጥ በሰው ልጅ ህይወት ይነግዳል። በተለይም በቅርቡ ህጻናትን እና ወጣቶችን ለሱዳን ወታደራዊ ግዳጅ በማቅረብ የፈጸመው አሳዛኝ ድርጊት፣ የፖለቲካ ነጋዴነቱን እና ጸረ-ሕዝብነቱን እርቃን ያወጣ ተግባር ነው።
ከዚህ የሰው ልጅ ንግድ ባለፈ፣ ቡድኑ የተፈጥሮ ሀብት ዝርፊያ ላይ የተካነ ስብስብ ነው። የሕዝብን አንጡራ ሀብት፣ በተለይም ወርቅ እና ሌሎች ማዕድናትን በህገ-ወጥ መንገድ ድንበር እያሻገረ በመሸጥ፣ ገንዘቡን በተለያዩ የውጭ ሀገራት ባንኮች ያከማቻል። ለዚህ ሁሉ የህገ-ወጥነት ተግባሩ ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር ሲል፣ ሆን ብሎ ማኅበራዊ እረፍትን ይነሳል። ሰላም እና መረጋጋት ካለ የኮንትሮባንድ እና የዝርፊያ መረቡ ስለሚበጠስ፣ አካባቢውን ቋሚ የጦርነት እና የስጋት ቀጣና አድርጎ ማስቀጠልን እንደ ዋነኛ የንግድ ስትራቴጂ ይጠቀምበታል።
የዚህ የፖለቲካ ገበያ እና ህገ-ወጥ አሠራር ሰለባ የሆነው ግን ምስኪኑ የትግራይ ሕዝብ ነው። የቡድኑ ቁንጮዎች በዝርፊያ ባካበቱት ሀብት በድሎት ሲኖሩ፣ ክልሉ ግን ዛሬም ድረስ በከፍተኛ የንጹህ መጠጥ ውሃ እጥረት፣ በመሰረተ ልማት ውድቀት እና በከፋ ድህነት ውስጥ ይገኛል። እናቶች ልጆቻቸውን ለትርጉም አልባ ጦርነት እየገበሩ፣ በማያባራ የሀዘን ማጥ ውስጥ እንዲኖሩ ተፈርዶባቸዋል። የሕዝቡ እረፍት ማጣት፣ ረሃብ እና መፈናቀል ለቡድኑ መሪዎች የንግድ ትርፍ ማካበቻ እና የሥልጣን ዕድሜ ማራዘሚያ ሆኖ ቆይቷል።
ሆኖም፣ ይህ በደም እና በዝርፊያ ላይ የተገነባ የፖለቲካ ገበያ ዛሬ ላይ ጣሪያው ፈርሷል። ሕዝቡ እና ወጣቱ የቡድኑን እውነተኛ የሽፍታ እና የነጋዴ ገጽታ በሚገባ ተረድተው፣ በአንድ ድምጽ "በቃኝ" ወደሚልበት ወሳኝ ምዕራፍ ተሸጋግረዋል። እራስን በነጻ አውጪነት የሰየመው ይህ እኩይ ስብስብ፣ የዘረጋው የኮንትሮባንድ እና የህገ-ወጥነት መረብ ከጫፍ እስከ ጫፍ እየተበጠሰ ነው።
ኢትዮጵያም ይህንን ጊዜው ያለፈበት የጥፋት ነጋዴ በሕዝቡ ትብብር እና ጽናት በማስወገድ፣ የዜጎቿን ሰላም እና የሀገርን ሉዓላዊነት አረጋግጣ የልማት ጉዞዋን ከማፋጠን የሚገታት ምንም ዓይነት ኃይል አይኖርም!
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: