የትግራይ ሕዝብ በረጅም የሀገራችን ታሪክ ውስጥ ለሰላም፣ ለፍትህ፣ ለነፃነት እና ለታላቋ ኢትዮጵያ አንድነት እጅግ ውድ ዋጋ የከፈለ ታላቅ ሕዝብ ነው። የሀገር ወዳድነትን ትርጉምና የነፃነትን ልዕልና ጠንቅቆ የሚያውቀው ይህ የተከበረ ሕዝብ፣ ለሀገሩ ሉዓላዊነት ቀዳሚ ጠባቂ ሆኖ የኖረ ነው።
ይሁን እንጂ፣ ይህ ለሀገር ደሙን ያፈሰሰና አጥንቱን የከሰከሰ ታላቅ ሕዝብ፣ ዛሬ ከራሱ አብራክ በወጡ፣ ነገር ግን የክህደት ካባ በደረቡ ልጆቹ መሪር ዋጋ እየከፈለ ይገኛል። ልክ ሙቀጫ በራሱ ዘነዘና እንደሚወቀጠው ሁሉ፣ የትግራይ ሕዝብም የራሱ ነን በሚሉ፣ ነገር ግን ከባዕዳን ጋር እያደሩና እየዋሉ የውጭ ጠላቶች ተልዕኮ አስፈጻሚ በሆኑ ክፉ ልጆቹ ያለርህራሄ እየተወቀጠ ነው።
በዚህ ህገወጥ የህወሓት ቡድን እኩይ ተግባር ምክንያት፣ የትግራይ እናት ዛሬም ዳግም ልታለቅስ፣ ዛሬም በከፍተኛ ስጋትና ፍርሃት ውስጥ ልትኖር ተገደዳለች። "ልጆቼ ደረሱልኝ፣ ብርቱ ከዘራ ሆኑኝ" ብላ በምትጽናናበት በዚህ ዘመን፣ ህገወጡ ቡድን እናቶችን ዳግም ወደማያባራ የሀዘን፣ የሰቆቃና የለቅሶ ማጥ ውስጥ ዘፍቋቸዋል። እነዚህ ምስኪን እናቶች፣ ለዘመናት በተራዘመ የፍርሃት እና የጭንቀት ስሜት ውስጥ ሆነው፣ ከጉያቸው ያሳደጓቸውን ልጆቻቸውን በከንቱ እየተነጠቁ ለመቀጠል ተገድደዋል።
ይህ እኩይ ቡድን ጦርነትን፣ ደም መፋሰስን እና ጀብደኝነትን እንደ ብቸኛ የመጨረሻ መፍትሄ አድርጎ የሚያይ፣ ከጦርነት ውጪ በሰላም መነጋገርን እንደ ትልቅ ኃጢያት የሚቆጥር የጥፋት ኃይል ነው። ዛሬም ከትናንት ባልተሻገረ የፖለቲካ እይታው፣ "ተከበናል፤ ሁሉም ይጠላናል" በሚል የጠላትነት ሥነ-ልቦና ሕዝቡን ማተራመሱን ቀጥሏል። ዛሬም በጨቋኝና ተጨቋኝ፣ በአጥፊና ተጠፊ የአረጀ ትርክት ውስጥ ታስሮ፣ የራሱን ጠባብ ኅልውና ለማስቀጠል ሲል ብቻ የትግራይን ወጣት በየጊዜው መግበሩን ሥራዬ ብሎ ተያይዞታል።
ስለልማት ማሰብ የተሳነው፣ የሕዝብን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር መፍታት የማይችለው ይህ ቡድን፣ ዛሬም የሚፎክር፣ የሚሸልል፣ ጠብመንጃ ነቅሶ ስለመግደልና ስለመሞት ወጣቱን የሚያዘጋጅ የአጉል ጥላቻ ሰባኪ ነው። ዛሬም እናቶች የጓዳቸውን ችግር የሚፈታላቸው ሳይሆን፣ የሞት ዜና የሚያረዳቸው ኃይል ነው የተጫናቸው።
በአንጻሩ የፌዴራል መንግሥት ለሰላም ያለውን ጽኑ ቁርጠኝነት በተግባር እያሳየ ይገኛል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቅርቡ በፓርላማ በነበራቸው ቆይታ፣ ስለ ሕዝብ እና ስለ ሀገር ሲባል፣ ከማናቸውም አካላት ጋር ለመነጋገር ፈቃደኛ መሆናቸውን በግልጽ አስገንዝበዋል።
ይህ የመንግሥት የሰላም ጥሪ ግን፣ በቡድኑ ዘንድ አዎንታዊ ምላሽ የለውም። ምክንያቱም ይህ ቡድን ሁልጊዜም ቢሆን ሙሉ በሙሉ ወደ ሥልጣን እስካልተመለሰ ድረስ፣ ሕዝቡን እንደ መያዣ በማድረግ በማሰቃየት እና በግጭት ውስጥ በመኖር የራሱን ጥቅም ማሳደድን የማይተው እኩይ ስብስብ በመሆኑ ነው።
ይሁን እንጂ፣ የጨለማው ዘመን እያበቃ ነው። መላው የትግራይ ሕዝብ፣ ከዚህ በሕዝብ ደም ከሚነግድ ቡድን አንዳች ምንዳም ሆነ የረባ ነገር እንደማይገኝ በሚገባ ተረድቷል። አሁንም ያልታበሰው የትግራይ እናቶች እንባ በእርግጠኝነት ይታበሳል። የትግራይ ወጣትም ከሞት ሩጫና ትንቅንቅ ተላቆ የሰላምን አየር ይተነፍሳል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: