"ለሊቱ ቀን ቀኑም ቀን ነው" የተባለላት ሻሸመኔ ከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴ የሚከናወንባት፣ በቀንም ሆነ በለሊት ሰዎች ለሥራ የሚሰማሩባት ደማቅ ከተማ ናት።
በ1913 ዓ.ም የተቆረቆረችው ሻሸመኔ፤ ስያሜዋን ያገኘችው ከአንድ በግል ንግድ ሥራ ላይ ከተሰማሩ ሻሼ ከሚባሉ ደግ እና እሩህሩህ እንደሆኑ ከሚነገርላቸው እናት ስም እንደሆነ የታሪክ አዋቂዎች ይገልጻሉ።
ከአዲስ አበባ በ255 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የምትገኘው ሻሸመኔ፤ በተለያዩ አቅጣጫዎች አምስት መውጫዎች ያሏት ሲሆን ከተሞችን በማገናኘት ከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴ ይካሄድባታል።
አሽከርካሪዎች እና መንገደኞች በከተማዋ አቋርጠው ሲያልፉ አረፍ የሚሉባት እና "ፀሐይ የማይጠልቅባት" የተባለችው ሻሸመኔ በርካታ ብሔር ብሔረሰቦችን ያቀፈች በብዙዎች ዘንድ የምትወደድ ከተማ ናት፡፡
ከተማዋ ለተለያዩ የውጪ ሀገራት ዜጎች በተለይም ለጃማይካውያን ቋሚ መኖሪያቸው በመሆን ትታወቃለች።
የከተማዋን እድገት የሚያፋጥኑ በፌዴራል ደረጃ እና በከተማ አስተዳደር የተለያዩ ፕሮጀክቶች እየተሰሩ ሲሆን ሆስፒታሎች፣ ትምህርት ቤቶች፣ መንገዶች እንዲሁም የተለያዩ መሰረተ ልማቶች ተገንብተው ለማህበረሰቡ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ።
በአሁኑ ወቅትም የሻሸመኔን ድምቀት የሚጨምር የኮሪደር ልማት ሥራ በስፋት እየተከናወነ ይገኛል።
ይህም የከተማዋን የንግድ እንቅስቃሴ ይበልጥ በማሳለጥ እድገቷን እንደሚያፋጥነው ይጠበቃል፡፡
በሔለን ተስፋዬ