Search

ከአንድ ችግኝ እስከ ቢሊዮኖች፦ በመደመር ዕሳቤ እየተጻፈ ያለው ታሪካዊው አረንጓዴ ዐሻራ

እሑድ ሐምሌ 26, 2018 85

የመደመር ዕሳቤ ያለፈውን በጎ ነገር እያጎለበቱ፣ ጉድለትን እያረሙ እና የወደፊቱን ብሩህ ተስፋ በጋራ ጥረት እውን የማድረግ ሒደት ነው።

ይህ ዕሳቤ በተግባር ከተገለጸባቸው እና የሕዝብን አቅም በአንድ ዓላማ ሥር ካሰባሰቡ ታላላቅ ሀገራዊ እንቅስቃሴዎች መካከል ደግሞ የአረንጓዴ ዐሻራ ጥረት በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል።

አረንጓዴ ዐሻራ የዛፍ ችግኞችን ከመትከል ያለፈ፣ የሀገራችንን ሥነ ምኅዳር የመመለስ፣ የተፈጥሮ ሀብትን የመንከባከብ እና የወደፊት ትውልድን አደራ የመወጣት ትልቅ ሀገራዊ ራዕይ መገለጫ ነው።

የመደመር ዕሳቤ ዋና ምሥጢር እያንዳንዱ ዜጋ በሚያበረክተው አስተዋጽኦ ውስጥ የሚፈጠርን ታላቅ ሀገራዊ አቅም ማሳየት ነው።

አንድ ዜጋ የሚተክላት አንዲት ችግኝ ከሚሊዮኖች ጥረት ጋር ስትደመር በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ችግኞች ይሆናሉ። ይህም የተራቆቱ ደኖችን ያንሰራራል፤ የአፈር መሸርሸርን ይከላከላል፤ የከርሰ ምድር ውኃንም ያበለጽጋል።

ይህ ዕሳቤ ሰዎችን ከተፈጥሮ ጋር ብቻ ሳይሆን፣ ዜጎችን በጋራ ዓላማ እና በጋራ የሥራ ባሕል እርስ በእርስ ያስተሣሥራቸዋል። በአንድ ጀምበር በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ተባብረው ችግኝ ሲተክሉ የሚታየው ኅብረት የዚሁ ሒደት ሕያው ማሳያ ነው።

ከአካባቢ ጥበቃ ባለፈ፣ የአረንጓዴ ዐሻራ እንቅስቃሴ ለምግብ ዋስትና መረጋገጥ እና ለሀገራዊ ኢኮኖሚ ዕድገት የጎላ አስተዋጽኦ አለው። የፍራፍሬ ችግኞች ተከላ፣ የደን ልማት እና የአግሮ ፎረስትሪ ሥራዎች የዜጎችን ገቢ ከማሻሻላቸው ባሻገር ለወደፊቱ አረንጓዴ ኢኮኖሚ መሠረት ይጥላሉ።

ይህንን በጎ ልምድ ለአጎራባች ሀገራት በመካፈልም ቀጣናዊ ትሥሥርን በማጠናከር፣ ዕሳቤው ከሀገር ወሰን ባሻገር ለአፍሪካ ቀንድ እና ለአህጉራዊ ወንድማማችነት እንዲተርፍ ተደርጓል።

አረንጓዴ ዐሻራ የዛሬን የተፈጥሮ ችግሮች ለመፍታት ብቻ ሳይሆን ለነገው ትውልድ የሚተላለፍ ዘላቂ ሀብት እና ቅርስ ነው።

አሁን ደግሞ በታሪክ አዲስ ምዕራፍ ለመጻፍ እና በአንድ ጀምበር 800 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል በተያዘው ታላቅ ሀገራዊ ጥሪ መሠረት የቀረው 1 ቀን ብቻ ነው።

ይህ ታላቅ ዕለት ሕዝባችን በሥራ፣ በተፈጥሮ እንክብካቤ እና በጋራ እሴት ላይ ተደምሮ የሀገር ሕልውናን እና ብልጽግናን ዳግም የሚያረጋግጥበት ታሪካዊ አጋጣሚ ይሆናል።

ዛሬ በጋራ ጥረት የምንተክለው እያንዳንዱ ችግኝ የነገዋን አረንጓዴ፣ ለም እና የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመገንባት የምናስቀምጠው የጽናት እና የፍቅር ዐሻራችን ነው።

በሔዋን ጌታቸው

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: