በዛሬው ዕለት ኢትዮጵያ በአንድ ጀምበር የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር 800 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል አቅዳ 805.3 ሚሊዮን ችግኞችን በመትከል ከዕቅዷ በላይ በማሳካት ድንቅ ውጤትን አስመዝግባለች።
ከማለዳው 12 ሰዓት ጀምሮ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከአንዱ የሀገራችን ጫፍ እስከ ሌላው በነቂስ በመውጣት እጁን ከአፈር ጋር አዋህዶ የነገዋን አረንጓዴ ኢትዮጵያ ሲተክል ውሏል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አረንጓዴ ዐሻራቸውን ባኖሩበት ወቅት፣ ዛፍ ተስፋ ነው፤ እየተተከለ ያለውም የነገ የልጆቻችን መጻኢ ዕድል ነው ብለዋል።
ይህ በዓይነቱ ልዩ የሆነ እና በአንድ ቀን ውስጥ 800 ሚሊዮን ችግኞችን የመትከል ግብ ያነገበው ሀገራዊ ንቅናቄ የበርካታ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎችን ትኩረት ስቧል፡፡
በዚሁም ኢትዮጵያ ባደረገችው ከፍተኛ ዝግጅት የመላው ሕዝቡን ንቁ ተሳትፎ ያጣመረ ስኬታማ ተከላ ማካሄዷን የቻይናው ሲጂቲኤን ዘግቧል፡፡
አልጄዚራ በበኩሉ፣ ይህ እንቅስቃሴ ኢትዮጵያ በፈረንጆቹ 2027 የምታስተናግደውን 32ኛውን የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP32) ዝግጅት በከፍተኛ ሁኔታ የሚያጠናክር መሆኑን አብራርቷል።
በተጨማሪም የደቡብ ኮሪያው ዘ ኮሪያ ፖስት "ተስፋን መትከል፤ የኢትዮጵያ አረንጓዴ ዐሻራ እና የሀገራዊ ለውጥ ኃይል" በሚል ርዕስ ባወጣው ጽሐፍ ዘመቻው ከአካባቢ ጥበቃ ባለፈ የሀገራችንን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሽግግር የሚያፋጥን ትልቅ ምሰሶ መሆኑን አመላክቷል፡፡
የሶማሊያው ሆርን ዲፕሎማት ደግሞ እንቅስቃሴው የደን መጨፍጨፍን ለመግታትና የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖዎችን ለመቋቋም ያለመ አርዓያነት ያለው ተግባር መሆኑን ገልጿል።
የኩባው ፕሬንሳ ላቲና ኢትዮጵያ ሌላ አዲስ ታሪካዊ ምዕራፍ ማብሰሯን ሲዘግብ፣ የፓኪስታኑ ኦሶዬትድ ፕሬስ የችግኝ ተከላው የሀገራችንን ዲፕሎማሲያዊ ገጽታ ያጎላ መሆኑንና በፓኪስታን የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲም የወዳጅነት ማጠናከሪያ ችግኝ መትከሉን አመልክቷል፡፡
እንዲሁም የዩጋንዳው ቻርማር እንደዘገበው፣ ይህ ዓመታዊ ንቅናቄ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለዘላቂ ልማትና ለአካባቢ ጥበቃ ትልቅ ማሳያና አርዓያ የሚሆን አዎንታዊ እርምጃ በመሆኑ ዛሬ የተተከሉት ችግኞች የአካባቢ ጥበቃ እንቅስቃሴ ብቻ ሳይሆኑ የኢትዮጵያውያን የአንድነት፣ የጽናትና የብልጽግና ተስፋዎች መሆናቸውን ያረጋግጣል።
በኢንቲሃድ አብራር
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: