Search

ከ90 ሚሊዮን ወደ 205 ሚሊዮን ኩንታል፦ የአማራ ክልል የግብርና ምርት ከእጥፍ በላይ ያደገበት ምሥጢር

እሑድ ሐምሌ 26, 2018 77

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከአሚኮ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ በለውጡ ማግሥት የአማራ ክልል ሕዝብ ካነሣቸው አንኳር የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ጥያቄዎች በመነሣት ክልሉ ከልማት አኳያ ይገባው የነበረውን ያህል ተጠቃሚ እንዳልነበር በጥናት መረጋገጡን አስታውሰዋል።

ይህ የልማት ክፍተት የክልሉ ብቻ ሳይሆን ሀገር አቀፍ ችግር እንደነበር ጠቅሰው፣ በአጭር ጊዜ ሙሉ ምላሽ ባያገኝም ባለፉት ጥቂት ዓመታት ግን ተስፋ ሰጪ እና የማይናቅ ርቀት መጓዝ መቻሉን ገልጸዋል።

በተለይም የጎንደርን ከፍተኛ የመጠጥ ውኃ ችግር ለመፍታት እና ለመስኖ ልማት ሲባል 18 ዓመታት ተጓትቶ የነበረው የመገጭ ግድብ ፕሮጀክት አሁን ላይ በመጠናቀቅ ላይ መሆኑን እና በቅርቡም አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር አብስረዋል።

በክልሉ ያሉ ግድቦችን ለማጠናቀቅ በቢሊዮን የሚቆጠር በጀት በመመደብ የተሠራው ሥራ እንዲሁም የተኬደበት ርቀት ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም ብለዋል።

ከግብርናው ዘርፍ አኳያ ከለውጡ በፊት በዓመት 90 ሚሊዮን ኩንታል ገደማ ብቻ ይመረትበት በነበረው የአማራ ክልል፣ አሁን ላይ ግድቦችን በማጠናቀቅ፣ ማዳበሪያ እና የግብርና ማሽነሪዎችን በማቅረብ እንዲሁም የውኃ ፓምፖችን በስፋት በማስገባት የተሠራው ጥረት ትልቅ ፍሬ አፍርቷል።

በዚህም የክልሉ ዓመታዊ ምርት ከእጥፍ በላይ በማደግ በአሁኑ ወቅት 205 ሚሊዮን ኩንታል በላይ መድረሱን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል።

ይህ ዕድገት እጅግ የሚያበረታታ ቢሆንም፣ በቂ ባለመሆኑ ገና በርካታ ሥራዎች እንደሚጠበቁ አጽንዖት ሰጥተዋል።

በአድማሱ አራጋው

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: