ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር ባደረጉት ቆይታ በታሪክ አጋጣሚዎች የተፈጠሩ የውስጥ ቅሬታዎች እና ኩርፊያዎች ከውጭ ኃይሎች ሴራ ጋር ሲጣመሩ የፈጠሩትን ሀገራዊ ጉዳትን አብራርተዋል።
በውስጥ ልዩነት እና በወቅቱ በነበረ የትስስር ችግር ምክንያት የተሄደበት መንገድ ኢትዮጵያ በዘመናት ስታስተዳድረው የነበረውን የቀይ ባሕር በር አጥታ ለዓመታት "የጂኦግራፊ እስረኛ" እንድትሆን ማድረጉን ገልጸዋል።
ይህ ታሪካዊ ጠባሳ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የንግድ እና የኢኮኖሚ መድረክ ላይ የሚገባትን ጥቅም እንዳታገኝ እና ለከፍተኛ የወደብ ኪራይ ወጪ እንድትዳረግ ያደረጋት ቢሆንም ኢትዮጵያ አሁን ላይ ያንን ሰንሰለት በጥሳ ለመውጣት አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ጀምራለች።
ኢትዮጵያ አሁን ላይ የቀይ ባሕር መብቷን ለማስከበር እና የታሪክ ስብራቱን ለመጠገን የያዘችው አቋም በተጨባጭ ሀገራዊ እና ቀጣናዊ እውነታዎች ላይ የተመሠረተ ነው።
ከ130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት እና ከምሥራቅ አፍሪካም አልፋ በአፍሪካ ደረጃ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት የምታስመዘግብ ሀገር በመሆኗ የቀጥታ የባሕር በር አለመኖሩ ለዘላቂ ዕድገቷ ትልቅ እንቅፋት በመሆኑ የባሕር በር ጥያቄ የህልውና ጉዳይ ሆንዋል ።
በተጨማሪም ኢትዮጵያ የቀይ ባሕር ባለቤትነቷን እና ተጠቃሚነቷን ለማረጋገጥ የምትከተለው መንገድ ሰላማዊ፣ የጋራ ዕድገትን ያማከለ እና ዓለም አቀፍ ህጎችን የተከተለ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ነው።
በጋራ የመልማት እና የመበልጸግ መርሕን በመከተል፣ ከአጎራባች ሀገራት ጋር በመነጋገር እና አቅሞችን በማስተሳሰር የታሪክ ስብራቱን ወደ አዲስ ኢኮኖሚያዊ ትስስር የመቀየር ሥራ እየተሠራ ይገኛል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ መልዕክትት እንደሚያመላክተው የትላንቱ የታሪክ ስህተት የተፈጸመው የውስጥ ጥንካሬን በማጣታችን እና ለውጭ ኃይሎች መጠቀሚያ በመሆናችን ነው።
ዛሬ ግን ኢትዮጵያ የውስጥ አንድነቷን እያጠናከረች በዲፕሎማሲ፣ በኢኮኖሚ እና በጂኦፖለቲካዊ ተፅዕኖዋ የጂኦግራፊ እስረኝነቷን ሰንሰለት በጥሳ የባሕር በር ባለቤትነቷን የምታረጋግጥበት ፅኑ መሠረት ላይ ትገኛለች።
ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር እጦት ምክንያት የኖረችበት የጂኦግራፊ እስረኝነት ዘመን እየተጠናቀቀ ነው።
አሁን የተያዘው ጽኑ ሀገራዊ አቋም የታሪክ ጠባሳውን በመሻር ለቀጣዩ ትውልድ የተከበረች እና ሙሉ የባሕር በር ባለቤት የሆነች ኢትዮጵያን ለማስረከብ ያለመ ታሪካዊ እርምጃ ነው።
በሃና ምንዳሁን
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: