Search

ማኅበረሰቡ ከዳር እስከ ዳር በኢትዮጵያዊነቱ ኮርቶ መኖር ይፈልጋል - ተመካካሪ ዳያስፖራዎች

እሑድ ሐምሌ 26, 2018 69

በኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ሂደት እየተሳተፉ የሚገኙ የዳያስፖራ ተመካካሪዎች ሂደቱ አባቶች እና እናቶች ያቆዩትን ሀገር በተሻለ መልኩ ወደሚቀጥለው ትውልድ ለማሸጋገር የሚያስችል ታሪካዊ ዕድል መሆኑን ገልጸዋል።

ተመካካሪዎቹ በሰጡት አስተያየት በምክክሩ ወቅት ያለፉ ትርክቶችን በማረም የጋራ የሆኑትን ይዞና መቅረት የሚገባቸውን አስቀርቶ ወደፊት ለመራመድ የሚያስችል ሰፊ የውይይት መድረክ መፈጠሩን ጠቁመዋል።

ይህም የሁሉንም ድምፅ በመስማት ለሀገር እና ለዓለም ሰላም የምትበጅ ፅኑ ኢትዮጵያን ለመገንባት ትልቅ መሠረት እንደሚጥል እምነታቸውን ገልጸዋል።

ከዚህ ቀደም የሀገረ መንግሥቱ መተዳደሪያ ደንቦች እና ሕገ-መንግሥት የሚፃፉት በፖለቲከኞች ብቻ እንደነበር ያስታወሱት ተመካካሪዎቹ አሁን ግን ሕዝቡ ከየአቅጣጫው ተሰብስቦ በዚህ ብንተዳደር ይሻለናል የሚለውን ሀሳብ የመስጠት ዕድል ማግኘቱ በታሪክ ታይቶ የማይታወቅ አዲስ ተሞክሮ መሆኑን አብራርተዋል።

በሕዝቡ ሙሉ ድምፅ የሚዘጋጅ መተዳደሪያ ደንብ አልተደመጥኩም የሚል ወገን የሌለባትን እና በሁሉም ዘንድ ቅቡልነት ያላትን ኢትዮጵያን ለመፍጠር የሚያስችል ከምንም በላይ ትልቅ አጋጣሚ መሆኑ ተመላክቷል።

በየአካባቢው ባለው እንቅስቃሴ ማኅበረሰቡ ከዳር እስከ ዳር በኢትዮጵያዊነቱ ኮርቶ መኖር የሚፈልግ መሆኑን እንደታዘቡ የተናገሩት ተመካካሪዎቹ ይህም ለኢትዮጵያ ተስፋ ሰጪ እንደሆነ ገልጸዋል።

ሕዝቡ እርስ በርስ የሚተጋገዝበት፣ ከአንዱ አካባቢ ወደ ሌላው ተንቀሳቅሶ እና ሀሳብ የሚያንሸራሽርበት ምህዳር መስፋቱ የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ዕድገት እና ሁለንተናዊ ጉዞ በእጅጉ እንደሚያፋጥነው ያላቸውን ፅኑ እምነት አረጋግጠዋል።

በሃና ምንዳሁን

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: