የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ በሀገሪቱ ታሪክ አዲስ የምክክር ባህልን የከፈተ ታሪካዊ ዕድል መሆኑን የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ገለጹ።
ተመካካሪዎቹ በጉባኤው ላይ የግልና የቡድን ፍላጎቶችን ወደ ጎን በመተው፣ ሀገራዊ ጥቅምን ባስቀደመና በሃሳብ ልዕልና ላይ በተመሠረተ መልኩ ነፃና አሳታፊ ውይይት እየተካሄደ ይገኛል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ተወካይ አቶ ጣሂር መሐመድ ጉባኤው ሀገርን ወደ ተሻለ ምዕራፍ የሚያሸጋግር መሆኑን ጠቅሰዋል።
በዋናው ጉባኤ ላይ በሚቀርቡ ዐበይትና ንዑሳን አጀንዳዎች ዙሪያ ተሳታፊዎች በነፃነትና በአካታችነት እየተመከሩ መሆኑን ገልጸው፣ ይህም የኢትዮጵያን መሠረታዊና መዋቅራዊ ችግሮች በሃሳብ የበላይነት በመፍታት ሀገራዊ መግባባትን ለማምጣት ጉልህ ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረዋል፡፡
ሌላው የምክክሩ ተሳታፊ የትግራይ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ትዴፓ) ሊቀመንበር ዶ/ር አረጋዊ በርሔ፤ ጉባኤው የመደማመጥና የመግባባት ባህልን በሚያጎለብት መልኩ በከፍተኛ አሳታፊነት እየተካሄደ መሆኑን አስታውቀዋል።
ከአጀንዳ ማሰባሰብ እስከ ተሳታፊዎች ልየታ ድረስ ያለው ሂደት አካታች መሆኑን ያወሱት ዶ/ር አረጋዊ፤ ከአራቱም የሀገሪቱ ማዕዘናት የተውጣጡ አራት ሺህ ተሳታፊዎች ሃሳባቸውን በነፃነት እያንሸራሸሩ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህ ሂደት ሀገራዊ ችግሮችን በሰለጠነ መንገድ ለመፍታትና ዘላቂ መግባባት ላይ ለመድረስ የተፈጠረ ታሪካዊ ዕድል መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃ አውጪ ግንባር (ኦብነግ) አባል አቶ ሙሐሙድ መሐመድ ሀሰን፤ አራት ሺህ የሕዝብ ወኪሎች የኢትዮጵያን ብዝኅነት፣ ሕብረ-ብሔራዊ እሴቶችና የጋራ ሀገራዊ ጥቅሞችን በሚያንጸባርቁ ጉዳዮች ላይ እንዲመክሩ መድረኩ ዕድል መፍጠሩን አብራርተዋል።
ሀገራዊ አለመግባባቶችን በጦር መሣሪያና በኃይል ለመፍታት መሞከር አዋጭ እንዳልሆነ በማስገንዘብ፣ በጉባኤው አዲስ ታሪክ እየተጻፈና ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ የመግባባት ምዕራፍ የሚያሸጋግሩ አጀንዳዎች እየተነሱ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የቁጫ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ፕሬዝዳንት አቶ ገነነ ገረቡ በበኩላቸው፤ በጉባኤው አንዱ የሌላውን ሃሳብ ለመረዳት በሚያስችል መልኩ ማንኛውም የሕዝብ አጀንዳ በነፃነት እየተንጸባረቀ መሆኑን ገልጸዋል።
የውይይት መድረኩ ለዘመናት የቆዩ አለመግባባቶች ወደ ቀጣዩ ትውልድ እንዳይተላለፉ የሚያስችልና በአርአያነት የሚወሰድ ነፃና የሰለጠነ የምክክር ሂደት እየተካሄደበት መሆኑን መስክረዋል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: