ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር ባደረጉት ቆይታ በአማራ ክልል እየተከናወኑ ያሉ ታላላቅ የልማት ፕሮጀክቶችን በተመለከተ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ከእነዚህ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች መካከል የጎንደር ከተማ ነዋሪዎችን የረዥም ዘመን የመጠጥ ውኃ ጥያቄ የሚመልሰው እና ሰፊ የመስኖ ልማት አቅም ያለው የመገጭ ግድብ በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል፡፡
ግንባታው በ2001 ዓ.ም. የተጀመረው ይህ ግድብ፣ ላለፉት 18 ዓመታት የመልካም አስተዳደር እና የፕሮጀክት አመራር ድክመት ተጓትቶ ቆይቷል፡፡ ይሁን እንጂ በ2017 በጀት ዓመት በጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀጥተኛ አመራር፣ አፈጻጸሙ ዝቅተኛ የነበረው ተቋራጭ ከፕሮጀክቱ እንዲወጣ ተደርጎ ሥራው ለሀገር በቀል ተቋራጭ ተሰጥቷል፡፡
የውጭ ከፍተኛ ባለሙያዎች ተጋብዘው የመሬት መንሸራተት ችግሩ በጥናት እንዲፈታ መደረጉ፣ እንዲሁም ሥራው በቀን እና በሌሊት ፈረቃ እንዲከናወን መወሰኑ ፕሮጀክቱን ከእንቅልፉ ቀስቅሶ ወደ ጤናማ እና ፈጣን የአፈጻጸም ምዕራፍ አሸጋግሮታል፡፡
በዚህም የግንባታው ወሳኝ ምዕራፍ የሆነው የወንዝ ቅልበሳ ሙሉ በሙሉ የተጠናቀቀ ሲሆን፣ ፕሮጀክቱ በቅርቡ ለፍሬ እንደሚበቃ ይጠበቃል፡፡
የመገጭ ግድብ ከግንባታ ባለፈ የኢትዮጵያውያን የልማት ፅናት ማሳያ ነው፡፡ አጠቃላይ የውኃ መያዝ አቅሙ 185 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 116 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር የሚሆነው ለመስኖ ልማት የሚውል ነው፡፡
ይህም 17 ሺህ ሔክታር መሬትን በመስኖ በማልማት የጎንደር ከተማን እንዲሁም የምሥራቅ እና የምዕራብ ደምቢያ አካባቢ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ያደርጋል፡፡
ክልሉ ያለውን ሰፊ የውኃ እና የመሬት ሀብት አቀናጅቶ ለመጠቀም እየተገነቡ ካሉ ሰፋፊ የመስኖ አውታሮች አንዱ የሆነው ይህ ፕሮጀክት፣ የሀገራችን የግብርና ትራንስፎርሜሽን እና የምግብ ዋስትና ራዕይ በጉልህ የሚያሳካ የዘመን ትሩፋት ነው፡፡
ይህ የኢትዮጵያ የማይቆም የልማት እርምጃ እንደተለመደው የግብፅ ሚዲያዎችን ሰላም ነስቷል፡፡
የመገጭ ግድብ በጣና ሐይቅ ገባር ወንዝ ላይ የሚገነባ መካከለኛ ፕሮጀክት ቢሆንም፣ የግብፅ ሚዲያዎች ፕሮጀክቱን በተመለከተ ሰሞኑን እያስተጋቡት ያለው ጩኸት ሀገሪቱ ከያዘችው የቆየ እና ራስ ወዳድ የውኃ ፖሊሲ የሚመነጭ ነው፡፡
ግብፅ ኢትዮጵያ የውኃ ሀብቷን እንዳትጠቀም የማስፈራራት ፖሊሲን ብትከተልም፣ ኢትዮጵያ ግን ታላቁን የሕዳሴ ግድብ አጠናቅቃ ልማቷን የሚያፋጥኑ እንደ መገጭ ያሉ ግድቦችን መቀጠ "ኢትዮጵያ አትጨበጥም" የሚል ድንጋጤ ፈጥሮባቸዋል፡፡
ግብፅ አሁንም ጊዜ ያለፈባቸውን የቅኝ ግዛት ውሎች እያነሳች የትኛውም የኢትዮጵያ ልማት ግብርናዋን እንደሚጎዳ በማስመሰል ከእውነት የራቀ ኢ-ፍትሐዊ ትርክት ታራምዳለች፡፡
ኢትዮጵያ ግን ፍትሐዊና ምክንያታዊ የውኃ አጠቃቀም መርህን (CFA) በመከተል ሕዝቧን ለመመገብ የገዛ ሀብቷን የማልማት ተፈጥሯዊና ሕጋዊ መብቷን እያስከበረች ትገኛለች፡፡
ከዚህም ባሻገር እንደ መገጭ ባሉ የኢትዮጵያ ደጋማ ቦታዎች ግድብ መሥራት የውኃ ትነትን እጅግ የሚቀንስ መሆኑ የኢትዮጵያ ልማት ማንንም የማይጎዳ ለመሆኑ ሳይንሳዊ ማረጋገጫ ነው፡፡
እውነታው ኢትዮጵያ አሁን ያለችበት ምዕራፍ ከትላንቱ በእጅጉ የተለየ መሆኑ ነው፡፡ ሀገራችን የዜጎቿን ሕይወት ለመለወጥ እና ከድህነት ለመውጣት የምታደርገውን የልማት ጉዞ በማንኛውም የውጭ ኃይል እጅ ጥምዘዛ የማታቆምበት ታሪካዊ ከፍታ ላይ ትገኛለች፡፡
የመገጭ ግድብም ሆነ ሌሎች በሀገራችን እየተከናወኑ ያሉ የልማት ፕሮጀክቶች የዚሁ ሉዓላዊ መብት አካል ናቸው፡፡
ማንም ይጩህ ማን፣ ኢትዮጵያ በራሷ ሀብት፣ በራሷ አቅም እና በራሷ ጊዜ የጀመረቻቸውን የልማት ሥራዎች ከዳር በማድረስ ታሪኳን በአዲስ መልክ መጻፏን አጠናክራ ትቀጥላለች፡፡
መንግሥትም በቀጣይ የመገጭ ግድብ ቀሪ ሥራዎችን በተያዘላቸው ጊዜ በማጠናቀቅ፣ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራዎችን በማጠናከር እና በዓለም አቀፍ ደረጃ የዲፕሎማሲ ሥራውን በማስፋት የኢትዮጵያን ብልጽግና ያረጋግጣል፡፡
በለሚ ታደሰ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: