Search

ከ2 ሺህ ወደ 4 ሺህ 500 ኪሎ ሜትር: በአማራ ክልል የተመዘገበው ግዙፍ የመሠረተ ልማት እድገት

እሑድ ሐምሌ 26, 2018 101

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) በአማራ ክልል የተመዘገቡ የልማት ስኬቶችን በተመለከተ ከአሚኮ ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ በክልሉ ከለውጡ በፊት 2 ሺህ ኪሎ ሜትር ገደማ የነበረው የመንገድ ሽፋን አሁን ላይ ከእጥፍ በላይ በማደግ 4 ሺህ 500 ኪሎ ሜትር መድረሱን ተናግረዋል።

ምንም እንኳን በክልሉ የጸጥታ ችግሮች፣ ዘረፋዎች እና የሥራ ማስቆሞች ቢያጋጥሙም፣ በአሁኑ ወቅት 61 ገደማ የመንገድ ፕሮጀክቶች በመከናወን ላይ መሆናቸውን እና ከእጥፍ በላይ መንገድ መሠራቱን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል።

ለዚህም ማሳያ በባሕር ዳር ከተማ ለእይታ ማራኪና ለአገልግሎት እጅግ ጠቃሚ የሆኑ እንደ አዲሱ የዓባይ ድልድይ ያሉ መሠረተ ልማቶች መገንባታቸውን አንስተዋል።

የአቪዬሽን መሠረተ ልማትን በማስፋፋት በደብረማርቆስ አዲስ የአውሮፕላን ማረፊያ ተገንብቷል።

የባሕር ዳር ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አዲስ ተርሚናልም ከቦሌ ቀጥሎ በኢትዮጵያ ሁለተኛው ትልቁ ሆኖ የተሠራ ሲሆን፣ የኮምቦልቻ ተርሚናል ግንባታም በተሳካ ሁኔታ ተጠናቋል።

ከመጠጥ ውሃ አቅርቦት አኳያም ከፍተኛ ችግር በነበረባቸው እንደ ሰሜን ወሎ ባሉ የተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች ሰፊ የውሃ ፕሮጀክቶች ተሠርተው ለሕዝቡ አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ።

በጤናው ዘርፍም አስደናቂ ለውጥ ታይቷል። ከለውጡ በፊት በመላው ክልሉ 5 ብቻ የነበሩት ጠቅላላ ሆስፒታሎች በሦስት እጥፍ በማደግ 20 የደረሱ ሲሆን፣ 43 የነበሩት የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎች ደግሞ 87 ደርሰዋል፤ ከዚህም በተጨማሪ በርካታ አዳዲስ ጤና ጣቢያዎች ተገንብተዋል።

በኤርፖርት፣ በመንገድ፣ በኢንዱስትሪ፣ በቱሪዝም እና በግድብ ግንባታ በአማራ ክልል የተሠራው ሥራ ባለፉት ሃያ እና ሠላሳ ዓመታት ከተሠራው የላቀ መሆኑንና ይህንንም አራክሶ ማየት ፈጽሞ እንደማይቻል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል።

በአድማሱ አራጋው

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: